የአለማችን የእድሜ ባለጸጋ በ117 አመታቸው ህይወታቸው አለፈ
ማሪያ ብራኒያስ ከአንደኛው የአለም ጦርነት እስከ ኮሮና ቫይረስ ድረስ ትላልቅ አለምአቀፋዊ ሁነቶችን መመልከት ችለዋል
የእድሜ ባለጸጋዋ ከመርዛማ አስተሳሰብ መራቃቸው ለእድሜያቸው መርዘም ምክንያት መሆኑን ገልጸው ነበር
የአለም በእድሜ ትልቋ ሴት ማሪያ ብራኒያስ 117ኛ አመታቸውን ባከበሩ አምስተኛ ወራቸው ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል፡፡
የእድሜ ባለጸጋዋ ቤተሰቦች በሚያስተዳድሩት የኤክስ (ትዊተር) ገጽ “ማሪያ እንደምትመኘው ያለ ምንም ስቃይ ሰላም በተሞላበት መንገድ በእንቅልፍ ውስጥ እንዳለች ሞት ወስዷታል” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
በ1907 በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ የተወለዱት ማርያ በመጀመርያው የአለም ጦርነት ጅማሮ ነበር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ስፔን አቅንተው በዚያው ኑሯቸውን ያደረጉት፡፡
በ23 አመታቸው በትዳር ከተጣመሯቸው ባለቤታቸው 3 ልጆችን የወለዱት የእድሜ ባለጸጋዋ 11 የልጅ ልጅ እና 13 የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል፡፡
ትውልድ አሜሪካዊ ስፔናዊቷ አዛውንት ያለፉትን ሁለት አስርት አመታት በሰሜን ምስራቅ ስፔን በሚገኝ የአረጋውያን ማቆያ ውስጥ ያሳለፉ ሲሆን 117ኛ አመት ልደታቸውን ባለፈው መጋቢት አክብረው ነበር፡፡
የህክምና ባለሙያዎች ማርያ በሚገኙበት አድሜ በነበራቸው አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤንነት እንደሚደነቁ ይነገራል፡፡ በ105 አመታቸው ፒያኖ እንደሚጫወቱ ፣ ጋዜጣ እንደሚያነቡ እና ሁሌ ጠዋት ጠዋት የአካል ቃት እንቅስቃሴ ያደርጉም እንደነበር ነው የተገለጸው።
በኤክስ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ከ16 ሺ በላይ ተከታዮች ያሏቸው ማርያ ለመጨረሻ ጊዜ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ጊዜው ቀርቧል የድካም ስሜት እየተሰማኝ ነው፤ ስለኔ እንዳታለቅሱ ራሳችሁንም እንዳትጎዱ የትም ብሄድ ደስተኛ እንደምሆን እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ጽፈው ነበር፡፡
117 አመታትን በምድር ላይ የኖሩት ማሪያ ብራኒያስ በእድሜ ዘመናቸው የምድርን ቅርጽ የለወጡ እና በታሪክም ከፍተኛ ሁነት ተደርገው የሚቀመጡ ክስተቶችን ለመመልከት ችለዋል፡፡
ከነዚህ መካከል የመጀመሪያው እና ሁለተኛው የአለም ጦርነት ፣ የ1918ቱ ስፓንሽ ፍሉ ፣ የሂሮሽማ እና ናጋሳኪ የአቶሚክ ቦንብ እልቂት ፣ ከ1941 – 45 የዘለቀው የአይሁዶች ጭፍጨፋ ፣ የሰውን ልጅ ለመጀመርያ ጊዜ ጨረቃ መርገጥ ፣ የሶቭየት ህብረት መፍረስ እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይጠቀሳሉ፡፡
የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በ2023 ጥር ወር ላይ በህይወት የሚገኙ በእድሜ ትልቋ ሰው ክብረ ወሰንን ሰጥቷቸው ነበር፡፡
ግለሰቧ እውቅናውን ያገኙት ከእርሳቸው በአንድ አመት የሚበልጡት ፈረንሳዩ የ118 አመት ባለጸጋ ሉሲል ራነደን መሞታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ከማርያ ህልፈት በኋላ በህይወት ያለ የአለም በእድሜ ትልቁ ሰው ክብረወሰንን ጃፓናዊቷ የ116 አመት ባለጸጋ ቶሚኮ ኢቶካ የሚረከቡ ይሆናል፡፡
እስካሁን በምድር ላይ ረጂም ጊዜ የቆዩት ሰው ጄን ሉዊስ ክሊመንት የተባሉት የ122 አመት ከ164 ቀን እድሜ ባለጸጋ ነበሩ፡፡