በ57 አመት የሚበልጧትን አዛውንት ያገባቸው ቻይናዊ ወጣት ተቃውሞው በርትቶባታል
የ23 አመቷ ወጣት ግን የአዛውንቱ የህይወት እወቀትና መረጋጋት ከወንዶች ሁሉ እንድመርጣቸው አድርጎኛል ብላለች
የእድሜ ልዩነቱ መስፋት መነጋገሪያነቱ ቢቀጥልም ጥንዶቹ በደስታም በሀዘንም ላይነጣጠሉ ቃል ተገባብተው ጎጆ ቀልሰው መኖር ጀምረዋል
የ23 አመቷ ቻይናዊት እና የ80 አመት አዛውንት በትዳር መጣመር የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገርያ ሆኗል።
በቻይናዋ ሄቢ አውራጃ ነዋሪ የሆነችው ሻውፋንግ የህይወት አጣማሪዋን ሊ ያገኘቻቸው በአዛውንቶች ማቆያ በበጎፈቃድኝነት እያገለገለች በነበረበት ወቅት ነው፡፡
ቀስበቀስ ተቀራርበው ጓደኛማቾች መሆን የቻሉት ሻውፋንግ እና ሊ ግንኙነታቸው ወደ ፍቅር አድጎ በቅርቡም በትዳር ተሳስረዋል።
የፍላጎቶቻቸው መመሳሰል የሚስተር ሊ ብስለት ፣ የህይወት ልምድ እና መረጋጋት በአዛውንቱ ፍቅር እንድትወድቅ እንዳደረጋት ሻውፋንግ ትናገራለች፡፡
በሁለቱ ጥንዶች ያልተለመደ የፍቅር ግንኙነት የተቆጡት የሻውፋንግ ቤተሰቦች ልጃቸውን አይንሽን ላፈር ብለው ርቀዋታል።
= ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ ዘመድ እና ጉዳዩን ከሰሙ ሁሉ የሚደርስባት ጫና ከውሳኔዋ ወደኋላ ያላስበላት ሻውፋንግ በ57 አመት የሚበልጧትን ሊ ከአዛውንቶች ማቆያ አስወጥታ በአንድ ቤተ መኖር ጀምረዋል፡፡
የሁለቱን የፍቅር ግንኙነት በፎቶ እና በቪዲዮ የማህበራዊ ገጿ የምታጋራው ሻውፋንግ የመላ ቻይናዊያንን ቀልብ የሳበች ሲሆን ተከታዮቿም በሁለት ተከፍለው በጉዳዩ ላይ እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡
ወጣቷ በርካታ አማራጭ እያላት ሀብት ወይም ገንዘብ ከሌላቸው በጡረታ ገንዘብ ከሚኖሩ አዛውንት ጋር ህይወት ለመመስረት ማሰቧ ንጹህ አፍቃሪ መሆኗን ያሳያል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፥ በተቃራኒው ወጣቷ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ እና ለመታወቅ ያደረገችው ነው በሚል የተቃወሟትም በርካታ ናቸው፡፡
በመካከላቸው ያለው የእድሜ ልዩነት ተፈጥሯዊ አይደለም በሚል የሚቃወሙ ሰዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ላይ ጉዳዩን አጀንዳ አድርገው እየተነጋገሩበት ነው፡፡
ሻው የተሰኘው የቻይና ድረ-ገጽ እንዳስነበበው ይህ ሁሉ ውዝግብ ባለበት ሁለቱ ጥንዶች በአነስተኛ ሰርግ በደስታም በሀዘንም አስከዘላለሙ ላይነጣጠሉ ቃል ተገባብተው ጎጆ ቀልሰው እየኖሩ ነው።