የ10 ዓመቱ ህጻን ከእናቴ ይልቅ ወላጅ አልባ ህጻናት ጋር ብኖር እመርጣለሁ ማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል
ይህ ህጻን የእናቴን የቤት ስራ ትዕዛዝ መቋቋም አልቻልኩም በሚል ፖሊሶች እንዲገላግሉት ጠይቋል
ህጻኑ በእናቱ ትዕዛዝ ተማርሬያለሁ በሚል ከወላጅ አልባ ህጻናት ጋር መኖር እፈልጋለሁ ማለቱ ተገልጿል
የ10 ዓመቱ ህጻን ከእናቴ ይልቅ ወላጅ አልባ ህጻናት ጋር ብኖር እመርጣለሁ ማለቱ ብዙዎችን አስገርሟል።
በቻይና አንድ የ10 ዓመት ህጻን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት ከእናቱ ጋር መኖር እንደማይችል አመልክቷል።
ህጻኑ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ያመራው የእናቱን የቤት ስራ ጥያቄ መቋቋም አልቻልኩም በሚል እንደሆነ ተገልጿል።
ይህ ህጻን ከሞኖሪያ ቤቱ በመውጣት ፊት ለፊቱ ወዳለ አንድ ፖሊስ ጣቢያ በማምራት ፖሊሶች ወላጅ አልባ ህጻናት ወደሚኖሩበት ስፍራ እንዲወስዱት ሲማጸን የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ብዙዎችም ይህን ተንቀሳቃሽ ምስል ካዩ በኋላ በህጻኑ ድርጊት መገረማቸውን፣ በቻይና ሰነፍ ትውልድ እየጨመረ መምጣቱን፣ ቀበጥ እና ሞልቃቃ ህጻናት እየበዙ መሆኑን ጽፈዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ህጻኑ ቅሬታውን እና ሀሳቡን ያቀረበበትን መንገድ ከማድነቅ ባለፈ የፖሊሶችን ድርጊት አሞግሰው አስተያየት ሰጥተዋል።
በሲሲቲቪ ካሜራ የተቀረጸው ይህ ምስል በብዙ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተጋራ ሲሆን ሁለት ፖሊሶች የህጻኑን ሀሳብ እና ፍላጎት ለማወቅ ሲጥሩ ታይተዋል።
ይህ ህጻን እናቱ ሁል ጊዜ የቤት ስራ እንዲሰራ እና እንዲያጠና እንደምታዘው እና ይህ ድርጊት እንደመረረው ህጻኑ ለፖሊሶች አስረድቷል ተብሏል።
በመሆኑም ህጻኑ ከቤት እንደወጣ እና ፍላጎቱም ወላጅ አልባ ህጻናት በሚኖሩበት ስፍራ አብሮ መኖር እንደሚፈልግ ለፖሊሶች ተናግሯል።
የህጻኑ እናት በልጇ ድርጊት መገረሟን አንድም ቀን እንዲህ ያደርጋል ብላ አስባ እንደማታውቅ መናገሯን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።