ለህክምና ወደ ሆስፒታል ለመጣ ህጻን አይስክሬም ያዘዘው ሀኪም ከስራው ተባረረ
የህጻኑ ቤተሰቦች የሐኪሙን ማዘዣ ፌስቡክ ላይ ማጋራታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል
ሐኪሙ ለህክምና የመጣውን ሕጻን ተጨማሪ ምርመራ ሳያደርግ አይስክሬም ውሰድበት ማለቱ ከስራ እንዲባረር ማድረጉ ተገልጿል
ለህክምና ወደ ሆስፒታል ለመጣ ህጻን አይስክሬም ያዘዘው ሀኪም ከስራው ተባረረ፡፡
በደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ባለ መንግስታዊ ሆስፒታል በህክምና ይሰራ የነበረ ሀኪም ያደረገው ድርጊት ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡
የ37 ዓመቷ ብራዚሊያዊት የ9 ዓመት ወንድ ልጇ ጉሮሮው አካባቢ ህመም አለው በሚል ነበር ወደ ሆስፒታል የወሰደችው፡፡
በሳኦፖሎ ከተማ ውስጥ ኦሳስኮ በተሰኘችው አካባቢ የሚኖሩት እናት ልጃቸውን ይዘው በአካባቢያቸው ወዳለ የመንግስት ሆስፒታል ያመራሉ፡፡
የህክምና ተራው ደርሷቸው ወደ ህክምና ክፍል ሲገቡም የህክምና አገልግሎት እየሰጠ የነበረው ሀኪም የልጃቸውን ህመም ለይቶ በፍጥነት የሚያድነውን መድሃኒት እንደሚያዝለት ይጠባበቃሉ።
ሐኪሙ ግን ህጻኑ ምኑን እንዳመመው ወላጅ እናቱንም ሆነ ህጻኑን ከመጠየቅ ይልቅ ህጻኑን አይስክሬም ትወዳለህ? ቪዲዮ ጌምስ? በማለት ይጠይቀዋል፡፡
ህጻኑም በደስታ አዎ እወዳለሁ ብሎ ይመልሳል፤ ሀኪሙም ህጻኑ አይስክሬም እንዲመገብ እና ቪዲዮ ጌም እንዲጫወት ሲል በህክምና ማዘዣው ላይ መጻፉ ተገልጿል፡፡
የህጻኑ እናት ሐኪሙ ህጻኑን የማከም ፍላጎት የለውም በሚል ወደ ቤታቸው ይመለሱ እንጂ የሐኪሙ ትዕዛዝ በርግጥም በመድሃኒት ማዘዣው ላይ መጻፉን አላስተዋሉትም ነበር፡፡
ጉዳዩን ለእህቶቿ ከነገሩ በኋላም የሐኪሙን ድርጊት ለማጋለጥ ትዕዛዙን በፌስቡክ ላይ ማጋራታቸውን ነው የሚያወሱት።
በዚህም ጉዳዩ በጥቂት ሰዓት ውስጥ በመላው ብራዚል መነጋገሪያ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡
በሀኪሙ ያልተገባ ድርጊት የተበሳጩ ብራዚሊያዊያን በሆስፒታሉ ላይ ትችቶችን መሰንዘራቸውን ተከትሎ ሀኪሙ ከስራ መታገዱን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡