የታሊባኑ ታሪካዊ መሪ ሙላህ ኦማር ከአሜሪካ ጥቃት ያመለጠበት "ማምለጫ መኪና" ከ20 ዓመታት በኋላ ለእይታ አቀረበ
ታሊባን መኪናው "ታላቅ ታሪካዊ ሃውልት" አድርጎ ለማሳየት በካቡል ብሔራዊ ሙዚየም ለማስቀመጥ ማቀዱ አስታውቋል
የታሊባን ባለስልጣናት ሚስጥር ቢያደርጉትም ሙላህ ኦማር እንደፈረንጆቹ በ2013 በተደበቁበት ህይወታቸው ማለፉ ይነገራል
ታሊባን የንቅናቄው ታሪካዊ መሪ ሙላህ መሀመድ ኦማር ከአሜሪካ ጥቃት ለመሸሽ የተጠቀመበትን መኪና ከ21 ዓመታት በኋላ ለእይታ አቀረበ፡፡
መኪናው ለእይታ የቀረበው በወቅቱ ከቀበሩት የታሊባን አመራሮች አንዱ የሆነው አብዱልጀባር አል ኦማሪ በሰጠው ትእዛዝ ነው ተብሏል፡፡
መኪናው ነጭ ቶዮታ ኮሮላ ሲሆን የተቀበረው በደቡባዊ ምስራቅ አፍጋኒስታን በዛቡል ግዛት በሚገኝ መንደር የአትክልት ስፍራ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
በዛቡል ግዛት የሚዲያ እና የባህል ዳይሬክተር ራህማቱላህ ሃማድ፤ መኪናው የፊቱ ክፍል በተወሰነ መልኩ ከመጎዳቱ በቀር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል፡፡
"መኪናው የተቀበረው እንደፈረንጆቹ በ2001 በታሊባን ታጣቂዎች ሲሆን የታሊባን ታሪካዊ መሪ ሙላህ መሀመድ ኦማርን ለማስታወስ በሚል ነበር" ሲልም አክሏል፡፡
የታሊባን ባለስልጣናት መኪናው ከትልቅ ጉድጓድ ውስጥ በአካፋዎች ተቆፍሮ ሲወጣ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ለቀዋል ።
ራህመቱላህ ሃማድ፡ ታሊባን መኪናውን "ታላቅ ታሪካዊ ሃውልት" አድርጎ ለማሳየት በዋና ከተማው ካቡል በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ለማስቀመጥ ማቀዱን ጠቁመዋል።
የታሊባን ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ይህ ሳምንት ሙላህ ኦማር ከካንዳሃርን በቶዮታ ኮሮላ የሸሹበት ታሪካዊ ሳምንት ነው፡፡
አሜሪካ ከሰፕቴምበር 11 ቀን 2001 ጥቃት በኋላ የታሊባን መሪውን ሙላህ መሀመድ ኦማር ስታሳድድ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
ምንም እንኳን የታሊባን ባለስልጣናት ለረጅም ጊዜ ደብቀውት የቆየ ሚስጥር ቢሆንም፤ የንቅናቄው ታሪካዊ መሪ እንደፈረንጆቹ በ2013 በተደበቁበት ህይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል፡፡
የታሊባን እንቅስቃሴ እንደፈረንጆቹ በ1996በካንዳሃር እንደተመሰረተ ይታወቃል፡፡
ንቅናቄው በተመሰረተ ማግስት አስገዳጅ የሸሪዓ ስርዓት በአፍጋናውያን ላይ ለመጫን ከመሞከሩ በዘለለ ሀገሪቱ ፤በሴፕቴምበር 11 ቀን 2001 የተፈጸመው ጥቃት መሃንዲስ የሆነውን የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን ጨምሮ የጽንፈኛ ቡድኖች መሸሸጊያ አድርግጓታል።
በዚህም ፤ ታሊባን ቢን ላደንን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አሜሪካ እና አጋሮቿ በሃገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍተው ከስልጣን እንዳባረሩት አይዘነጋም።
ያም ሆኖ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የትጥቅ ትግል ላይ የቆየው ታሊባን ባሳለፈነው ወርሃ ነሃሴ፣2021 ካቡልን እንደገና ተቆጣጥሮ ሀገሪቱን የሚመራበት በትረ ስልጣን መጨበጡ የሚታወቅ ነው፡፡