ታሊባን አፍጋናውያን ሴቶች ከዐይናቸው ውጭ ሙሉ በሙሉ መሸፈን አለባቸው ማለቱን ተከትሎ የጸጥታው ምክር ቤት ሊሰበሰብ ነው
አዋጁን ያወገዘው የጸጥታው ምክር ቤት ነገ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል
ታሊባን አዋጁን በማያከብሩ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል
ታሊባን አፍጋናውያን ሴቶች የፊት ገጽታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ልብስ (ቡርቃዓ) መልበስ አለባቸው ማለታቸውን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሊሰበሰብ ነው፡፡
ምክር ቤቱ ለነገ ሃሙስ ስብሰባ መጥራቱም ተሰምቷል፡፡
ታሊባን ባሳለፍነው ቅዳሜ ነበር በመካከለኛ እድሜ ላይ የሚገኙና እምብዛም እድሜያቸው ያልገፋ ሴት አፍጋናውያን እይታቸውን በማይካልል መልኩ የፊት ገጽታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ቡርቃዓ እንዲለብሱ ያወጀው፡፡
አዋጁ በሼሪዓ ህግ መሰረት የተላለፈ ነው፡፡ ከቅርብ ዘመዶቻቸው ውጭ ወንዶች ቢያገኟቸው እንዳይተናኮሷቸው በማሰብ የተላለፈ ነውም ነው የተባለው፡፡
አዋጁን አክብረው የማይገኙ በወንድ ዘመዶቻቸው ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ታሊባን አስታውቋል፡፡
ይህ ታሊባን ወደ ቀደመ ጥብቅ የአገዛዝ ይዞታው ለመመለሱ ማሳያ ነው በሚልም ለሴቶች መብት እንቆረቆራለን የሚሉ ብዙዎች አዋጁን እያወገዙት ይገኛሉ፡፡
“አፍጋኒስታን አሁን ነጻ እና ሉዓላዊ ሀገር ነች”- ታሊባን
ሁኔታው የአፍጋናውያን መብት ለማክበር ከአሁን ቀደም የተገባውን ቃል የሚያፈርስ ነው ያለው የተመድ የአፍጋኒስታን ተልዕኮም እጅጉን ያሳስበኛል ብሏል፡፡
ታሊባን ከ6 ሳምንታት በፊት ሴት የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርት የሚጀምሩበትን ጊዜ ማራዘሙና እርምጃው ዓለም አቀፋዊ ውግዘትን እንዳስከተለበትም ተልዕኮው አስታውሷል፡፡
ይህን ተከትሎ የድርጅቱ የጸጥታው ምክር ቤት በኖርዌይ ጠያቂነት ነገ ሃሙስ እንደሚሰበሰብም ነው የተገለጸው፡፡
የቀድሞው የአፍጋኒስታን የፋይናንስ ሚኒስትር በአሜሪካ የታክሲ ሹፌር መሆናቸው እያነጋገረ ነው
ታሊባን ከፈረንጆቹ 1996 እስከ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን እስከለቀቀበት እስከ 2001 ድረስ አፍጋኒስታንን መርቷል፡፡
በነዚህ ዓመታት የአፍጋኒስታን ሴቶች ቡርቃ እንዲለብሱ ይገደዱ እንደነበርም ይነገራል፡፡
ሆኖም የአሜሪካ ጦር መውጣቱን ተከትሎ የአሽራፍ ጋኒን መንግስት በማስወገድ ባሳለፍነው ወርሃ ነሐሴ መልሶ አፍጋኒስታንን የተቆጣጠረው ታሊባን የሴቶችን መብት ለማክበር ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡