የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የ50 አመት የፖለቲካ ጉዞ
በአሜሪካ ፖለቲካ በተለያዩ ዘርፎች ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸው ፖለቲከኛ ጉዞ በ90 ደቂቃ ክርክር ምክንያት ተጠናቋል
ከሴናተርነት ተነስተው እስከ አሜሪካ ፕሬዝዳንትነት የዘለቁት አዛውንቱ ፖለቲከኛ ከዘንድሮው ምርጫ እራሳቸውን አግልለዋል
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የ50 አመት የፖለቲካ ጉዞ
ለግማሽ ክፍለ ዘመን በተጠጋ ጊዜ በአሜሪካ ፖለቲካ ለውጥ ከፍተኛ አበርክቶ የነበራቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳነት ጆ ባይደን የፖለቲካ ጉዟቸው የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡
በ1972 በ29 አመታቸው ለሴናተርነት በመመረጥ በአሜሪካ ታሪክ በእድሜ ትንሹ ሴናተር ሲባሉ ከበርካታ አመታት በኋላ በእድሜያቸው መግፋት ምክንያት ከዕጩነት እንዲነሱ የሚጠይቁ ተጽእኖዎች በርትተው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አስገድደዋቸዋል፡፡
81 በመቶ አሜሪካውያን ባይደን ለሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመን አሜሪካን ለማስተዳደር ብቁ ናቸው ብለው እንደማያምኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የጆ ባይደን የ50 አመታት የፖለቲካ ስኬት እና ድክመቶች ምንድን ናቸው
የሴናተርነት ዘመን
በ1972 የዴልዌር ግዛት ሴናተር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ቀጣዮቹን 36 አመታት ወደ ዋሽንግተን እና ነጩ ቤተመንግስት የሚወስዳቸውን መንገድ በማቅናት አሳልፈዋል፡፡
በዴሞክራት ፓርቲ ሃላፊነት ቀስበቀስ በማደግ በፓርቲው ወሳኝ በሆነው የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኮሚቴን ለሁለት ጊዜ መርተዋል፡፡
ባይደን በሴናተርነታቸው ዘመን የተለያዩ ጠቃሚ የሚባሉ ህጎች እንዲወጡ እና እንዲተገበሩ ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡
የቤት ውስጥ ጥቃት ፣ ጾታዊ ጥቃት እና ሌሎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወንጀሎችን ለመከላከል የወጣውን ህግ እንዲጸድቅ በማድረግ እንዲሁም የጦር መሳሪያ የሚገዙ ሰዎች የኋላ ታሪካቸው እንዲጠና የሚያስገድደው ህግ እንዲጸድቅ የተወጡት ሚና ይጠቀስላቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለበርካታ ጥቁር አሜሪካውያን ለእስር እንዲዳረጉ ምክንያት ለሆነው በ1994 ለወጣው የወንጀል ህግ ላይ ፊርማቸውን በማኖር እንዲሁም ለ2003ቱ የኢራቅ ወረራ በመደገፍ እና የሌሎችን ድጋፍ በማስተባበር በነበራቸው አስተዋጽኦ ይተቻሉ፡፡
ለፕሬዝዳንት ለመወዳደር ያደረጓቸው ሙከራዎች
ባይደን በ2020 ተሳክቶላቸው የነጩ ቤተ መንግስት አዛዥ ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ ጊዜያት ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ጥረት አድርገዋል፡፡
በ1988 እና በ2008 ራሳቸውን የዴሞክራት እጩ አድርገው አቅርበው ከፓርቲው በቂ ድጋፍ ባለማግኝታቸው ወደፊት መምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በ2020 ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን ሲያሸንፉ ከተቀናቃኛቸው 7 ሚሊየን የሚበልጥ ድምጽ ማግኝት ችለው ነበር፡፡ የወቅቱ ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ምርጫው በድምጽ ቆጠራ ወቅት እንደተጭበረበረ በመግለጽ መሸነፋቸውን እንደማይቀበሉ አስታውቀው ነበር፡፡
በ2009 ወደ ሃላፊነት የመጡት የመጀመርያው ጥቁር የአሜሪካ መሪ ባራክ ኦባማ ምክትል በመሆን ለ8 አመታት ያገለገሉት ባይደን በነጩ ቤት መንግስት የፕሬዝዳንቱ ዋነኛ አማካሪ እና የቅርብ ሰው ሆነው ቆይተዋል፡፡
በነዚህ ጊዜያት የአሜሪካ ጦር ከኢራቅ እንዲወጣ እንዲሁም ከታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ ለአሜሪካ ግዛቶች የተሰጠው በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ በተገቢው መንገድ እንዲከፋፈል እና ሌሎች በኦባማ የተሰጣቸውን ትላልቅ ሃላፊነቶች በበቂ ሁኔታ መፈጸም ችለዋል፡፡
ባይደን በሴናተርነት ዘመናቸው የዴሞክራት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ኮሚቴን በመምራት የገነቡት ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እውቀታቸው እና ግንኑነታቸው በኦባማ እንዲመረጡ ካስቻላቸው ምክንያት መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
በዚህም በወቅቱ ወደ ተለያዩ የአለም ክፍሎች በመዘዋወር የኦባማ አስተዳደር ጠንካራ የውጭ ግንኙነት እንዲኖረው ሰርተዋል፡፡
ባይደን በ2016ቱ ምርጫ የኦባማ ተተኪ እንደሚሆኑ ከፍተኛ ግምት ቢያገኙም በወቅቱ በጭንቅላት ካንሰር ህይወቱን ባጣው ልጃቸው ሀዘን ላይ ስለነበሩ በውድድሩ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝደንትነት አራት አመታት
የባይደን አራት የስልጣን ዘመን ከመጀመርያው አሁን እስካለበት ጊዜ በበርከታ አለምአቀፋዊ ችግሮች የተሞላ ነበር፡፡
ኮቪድ 19 በእጅጉ የጎዳውን ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ሁኔታ ለማስተዳደር የተረከቡት ፕሬዝዳነቱ የወረርሽኙ ተጽዕኖ መቀዝቀዝ ሲጀምር የሩሲያ ዩክሬንን መውረር እንዲሁም እስራኤል በጋዛ ያወጀችው ጦርነት አስተዳደራቸው እንዲፈተን ካደረጉ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ከአራት አስርተ አመታት ወዲህ በአሜሪካ ከፍተኛ የተባለው የዋጋ ንረት፣ የስራ እድል ፈጠራ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲሁም የስደተኞች ጉዳይ ደግሞ በሀገር ውስጥ ጥልቅ ፈተናን ደቅነው የነበሩ ችግሮች ናቸው፡፡
ባይደን በአሜሪካ ያረጁ ድልድዮች እና የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለማደስ በጠየቁት በቢለየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የሪፐብሊክንን ጭምር ድጋፍ ያገኙ ሲሆን በመሳርያ ቁጥጥር አዋጅን ተግባራዊ በማድረግ እና በአሜሪካ የሚመረቱ የኮሚፒውተር ቺፖች መጠን እንዲጨምር ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታትም ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመከላከል በአካባቢ ጥበቃ ላይ በነበራቸው ጠንካራ አቋም 369 ቢሊየን ዶላር ከኮንግረሱ ያስፈቀዱበት ሂደትም ከስኬታቸው መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የሀማስ እና እስራኤል ጦርነትን የያዙበት መንገድ እንዲሁም በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ወሳኝ መፍትሄ ላይ አለመድረሳቸው ከሚወቀሱባቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡
ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የዘለቀው የባይደን የፖለቲካ በመጨረሻም ወደ መገባደዱ የተቃረበ ይመስላል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በኋላ የሚኖራቸው የፖለቲካ ጉዞ ምን እንደሚመስል በግልጽ ባይነገርም ከሚገኙበት የእድሜ ሁኔታ ጋር በተገናኝ ከፖለቲካው አለም እራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ሊያገሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡