አዲሱ የጦር መርከብ የፀረ አውሮፕላን ጨምሮ እስከ 250 ኪ.ሜ የሚያካልሉ ሚሳዔሎች ይታጠቃል
ከሰሞኑ የወጣ ምስል ቻይና በጣም ሚኒስጥራዊ በሆነ መንገድ አዲስ የሆነ የጦር መርከብ እየሞከረች መሆኑን አመላክቷል።
አዲሱ የቻይና የጦር መርከብ “እጅግ የላቀ” ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና “አስፈሪ” ከሚባሉ አውዳሚ ጦር መርከቦች መካከል እንደሚመደብ ነው የተነገረው።
ወታራዊ ጋዜጣ የሆነው ሚሊታሪ ዋች ጋዜጣ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ቻይና በአሁኑ ወቅት በጣም አውዳሚ የሚባለውን የጦር መርከብ እያመረተች ትገኛለች።
ሀገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥም በአንድ ዓመት ውስጥ እስከ 10 አውዳሚ የጦር መርከብ የማምረት አቅም እንደሚኖራትም ጋዜጣው አመላክቷል ።
ላለፉት አስርት ዓመታት “Type 052D እና Type 055” የተባሉ አውዳሚ የጦር መርከብ አይነቶች በብዛት ሲመረቱ የቆየ ሲሆን፤ ቻይና አሁን እየሞከረች ያለው ስቲልዝ የጦር መርከብ አይነት የወደፊት የጦር መርከቦች ምርት ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል ተብሏል።
የቻይና መገናኛ ብዙሃን ይዘው በወጡት መረጃ “አጠቃላይ የሙከራ ሂደት” በሚል በተሰየመው የሙከራ ወቅት ነው አዲሱ የቻይና መርከብ የታየው።
አዲሱ የቻይና መርከብ ከራዳር እይታ የሚያስመልጥ የራዳር መመከቻ ወይማ ማንጸባረቂያ መሳሪያ ያለው ሲሆን፤ በጦር መርከቦች ላይ የተለመዱ አይነት አንቴናዎችን አስቀርቷል።
97 ሜትር የሚረዝመው መርከቡ እምብዛም ያልተለመደ ባለ ነጠላ ማስወንጨፊያ የተገጠመለት ሲሆን፤ ይህም ከጠላት የሚለቀቁ “ኤሌክትሮ ኦፕቲካል” መሳሪያ እና ጠላት መሳሪያዎችን ለመከላከል የሚያስችል ነው።
መርከቡ ፀረ-አውሮፕላን ሚሳኤሎች ከ32 ማስወንጨፊያዎች ጋር የታጠቀ ሲሆን፤ ሚሳዔሉ እስከ 50 ኪ.ሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የጦር አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እና ክሩዝ ሚሳዔሎችን መምታት የሚችል ነው።
ፀረ-መርከቦች ሚሳኤሎችም መርከቡ ከታጠቃቸው የጦር መሳሪያዎች መካከል ሲሆኑ፤ እያንዳንዱ ሚሳኤል 165 ኪሎ ግራም አረር የሚይዝና እስከ 250 ኪ.ሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ጠላት ኢላማን መምታት የሚችል ነው።
እንዲሁም እንደ ሩሲያው ካሞቭ-28 ወይም ቻይናዊው ዜድ-9 ያሉ መካከለኛ ሄሊኮፕተሮችን መያዝ ይችላል።
ቻይና በሚስጥር እየገነባች ያለው ጦር መርከብ መቼ ወደ አገልግሎት የገባል በሚለው ዙሪያ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።