የአሜሪካ የጦር መርከብ በደበባዊ ቻይና ባህር ሉአላዊነቴን ተዳፍራለች ያለችው ቻይኛ ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ አዛለች
በደቡባዊ የቻይና ባህር ወደ ሚገኙ ደሴቶች በህገወጥ መንገድ ለመግባት የሞከረውን የአሜሪካ የጦር መርከብ ወደመጣበት መመለሷን ቻይና ገልፃለች።
የቻይና ደቡባዊ እዝ ቃል አቀባይ ቲያን ጁንሊ፥ ድርጊቱ የአሜሪካ ጦር የቻይናን ሉአላዊነት እየተፈታተነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለውታል።
የክሩዝ ሚሳኤል ተሸካሚ መርከቧ ህገወጥ እንቅስቃሴ በደቡባዊ የቻይና ባህር የአሜሪካን ቀንደኛ የደህንነት ስጋት ፈጣሪነትም እንደሚያመላክት ተናግረዋል።
ዋሽንግተን በባህሩ ዙሪያ የምታደርገው አሰሳ ዋነኛ አለማው ቀጠናውን የጦርነት ማዕከል ማድረግ ስለመሆኑም አንስተዋል ቃል አቀባዩ።
የቻይና ጦር ይህን ፀብ አጫሪ እንቅስቃሴ ለመመከት በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል ተብሏል።
የአሜሪካ ጦር ግን ከቻይና ለቀረበው ክስ የሰጠው ምላሽ የለም። ቻይና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የደቡባዊ ቻይና ባህር የግዛቴ አካል ነው ብላ ታምናለች።
አሜሪካ በበኩሏ የቻይና የግዛት ማስፋፋት ሩጫ የአለማችን ከ30 ከመቶ የወጪ ንግድ የሚተላለፍበትን መስመር በብቸኝነት እስከመቆጣጠር እየደረሰ ነው በሚል ትቃወመዋለች።
ሰው ሰራሽ ደሴቶችን እየገነባችም ወረራ እየፈፀመች ነው ስትል ቤጂንግን ትከሳለች።
አሜሪካ ከቅርብ አመታት ወዲህ ግዙፍ የጦር መርከቦቿ በደቡባዊ ቻይና ባህር መታየታቸውም ከዚሁ ክስ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።
ዛሬ ቻይና ወደመጣችበት መልሻታለሁ ያለቻት የአሜሪካ ሲጂ 62 መርከብ በቅርቡም በታይዋን ሰርጥ መታየቷ የሚታወስ ነው።
ከንግድ መስመርነቱ ባለፈ በአሳ ሀብቱ የሚታወቀው የደቡባዊ ቻይና ባህር የሃያላኑ መፋጠጫ ከሆነ ሰነባብቷል።