ለሃሳ የጦር መርከብ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎ የሚተኩስ 112 የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ሴሎች አሉት
ቻይና ካሏት የጦር መርከቦች ውስጥ አንዱ በሆነው ለሃሳ የጦረ መርከብ በጃፓን ባህር ላይ የረጅም ርቀት ልምምድ ማድረጓ ተገለፀ።
የኮሙኒስት ፓርቲ ጋዜጣ የሆነው ግሎበል ታይምስ ይዞት በወጣው ዘገባው፤ የቻይና ሁለተኛው ዓይነት 055 ትልቅ አውዳሚ የጦር መርከብ ባሳለፍነው ዓመት ስራ ላይ ከዋለ ወዲህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ግዙፍ የባሀር ላይ ልምምድ አድርጓል።
በልምምዱ ላይ ሉያንድ አይነት 052D እና ቼንግዱ አይነት 903 አውዳሚ የጦር መርከቦች መሳተፋቸውን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ሶስቱ የቻይና የጦር መርከቦች ነጋሳኪ ከሚገኘው ፉክ ደሴት በ200 ኪሎ ሜተር ርቀት ላይ መታየታቸውን አስታውቋል።
የቻይና ባህር ኃይል በጣም አስፈሪ በሆነ ሁኔታ በርካታ የጦር መርከቦችን እየገነባ ሲሆን፤ ባለው ጦር መርከብ ብዛትም ከዓለማችን ላይ ካሉ ግዙፍ የባህር ኃይሎች አንዱ መሆን ችሏል።
ቻይና ለሃሳ የተባለውን ሁለተኛው ዓይነት 055 ትልቅ አውዳሚ የጦር መርከብ ባሳለፍነው ዓመት ወደ ስራ ማስገባቷ ይነገራል።
“ለሃሳ” የሚል መጠሪያ ያለው ሁለተኛው ዓይነት 055 የጦር መርከብ 10,000 ቶን ደረጃ ያለው ሲሆን፤ የአየር ላይ እና የባህር ላይ ጥቃት እንዲሁም ፀረ-ባሕር ውስጥ የማጥቃት አቅምን ባሟላ መልኩ የሙሉ ኮርስ የውጊያ ሥልጠና ግምገማ ማለፉ ተነግሯል።
“ለሃሳ ዓይነት 055” የጦር መርከብ በዓለማችን ላይ ካሉ አደገኛ የጦር መርከቦች ውስጥ አንዱ እንደሚሆን ታምኗል።
መርከቡ 112 ወደላይ የሚሳዔል ማስወንጨፊያ ሴሎች ያሉት ሲሆን፤ በዚህም ከምድር ወደ ሰማይ ሚሳዔል ማስወንጨፍን ጨምሮ የምድር ላይ ጥቃት ሚሳዔሎችንን እንዲሁም የፀረ መርከብ እና የፀረ ሰርጓጄ መርከቦች ሚሳዔሎችንም ያስወነጭፋል።