ኢትዮጵያ 4 አደራዳሪዎች ይግቡ የሚለውን የሱዳን ሀሳብ አልቀበልም አለች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግስት ስለጉዳይ በይፋ እንዳልተገለጸለት አስታውቋል
ሱዳን አደራዳሪ ይሁኑ ላለቻቸው አራት አካላት የአደራድሩን ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት በግድቡ ጉዳይ በአደራዳሪነት ይግቡ የሚለውን ሀሳብ እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ስለጉዳዩ በይፋ እንዳልተገለጸለት ተናግረዋል፡፡
ሱዳን አደራዳሪ ይሁኑ ላለቻቸው አራቱ አካላት በይፋ ጥያቄ አቅርባለች፡፡
''የዛሬን አያድርገውና የሶስትዮሽ ድርድሩ የተበተነው ሱዳኖች የታዛቢዎች ሚና ከፍ ይበል ሲሉ ግብጾች አይሆንም ብለው ነበር'' ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡
ኢትዮጵያ አደራዳሪ ይሁኑ ከተባሉ አራቱም አካላት ጋር “መልካም ግንኙነት አላት፤ ግን መርህ ይከበር ነው ጥያቄያችን። ደቡብ አፍሪካ በደንብ ያስኬደችውን ድርድር ኮንጎ መጨረስ አለባት ነው የእኛ ሀሳብ” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ስለ አራቱ አካላት “እስካሁን የቀረበልን ጥያቄ የለም” ያሉት አምባሳደር ዲና , “ሱዳንን በሚመለከት ዝም ብንልም ፣ ለእኛም ወዳጅ ሀገራት እንዲሁም ለራሳቸውም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየገለጽን ነው” ብለዋል፡፡
“በምዕራባውያን የሚቀነቀነው ማዕቀብ፣ አድማ የሚለው ባዶ መዝሙር ነው ፤ የሚከፈላቸው ሚዲያ ተቋማት እና ግለሰቦች አሉ” ብለዋል አምባሳደር ዲና፡፡
ባለፈው ዓመት በግድቡ ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በአሜሪካ ዋሽንግተን በዓለም ባንክና በአሜሪካ ታዛቢነት ድርድር አካሄደው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በድርድሩ ወቅት የአሜሪካ ሚና ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ከዚያም ወደ ስምምነት ሰነድ አርቃቂነት አድጓል የሚል ምክንያት በማቅረቧ ድርድሩ ሊቋረጥ ችሏል፡፡
ከአሜሪካ ድርድር መልስ ሶስቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብርት አመቻችነትና በአሜሪካና በአውሮ ህብረት ታዛቢነት ድርድሩ እዲካሄድ ተስማምተው ነበር፤ በርካታ የድርድር ዙሮችም ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡