“ባለን አጭርጊዜ በግድቡ ጉዳይ ከስምምነት ላይ መድረሱ የግድ ነው”- አብደላ ሃምዶክ፣የሱዳን ጠ/ሚ
ድርድሩ በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ዴሞክራቲክ ኮንጎ እንዲመራ ሃገራቱ በቅርቡ መስማማታቸው የሚታወስ ነው
የግድቡ ጉዳይ በተራዘመ የዲፕሎማሲ ድርድር ምክንያት እስካሁን መፍትሄ ያልተበጀለት አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል
በህዳሴው ግድብ ዙርያ ሶስቱም ሀገራት በሚያደርጉት ድርድር ከስምምነት መድረስ አለባቸው ሲሉ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው እለት ከግብፁ አቻቸው ሙስጠፋ ማድቡሊ ጋር በካይሮ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ሀገራቱ በግድቡ ጉዳይ ከስምምነት መድረሳቸው የተሻለ ነው ያሉት ሃምዶክ የሁሉንም ሀገራት ጥቅም የሚያስጠብቅ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
“ባለፈው አመት በወርሀ ሃምሌ ኢትዮጵያ በተናጠል ስትወስንና ሙሌት ስታካሂድ ተመልክተናል፡፡ አሁንም በመጪው ሃምሌ ተመሳሳይ ሙሌት ልታካሂድ እንደሆነ አዝማሚያዎችን እያየን ነው፤ እናም አሁን ያለን ጊዜ አጭር እንደመሆኑ ከስምምነት መድረሱ ግድ ይላል በዚህም ተስፋ አለኝ”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
የግብጹ አቻቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የመልማት እቅድ ግብፅ አትቃወምም፤ ይሁን እንጂ ልማቱ ሱዳንና ግብፅን ጨምሮ የታችኛው ሀገራት ጥቅምን የሚነካ መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡
ማድቡሊ ከስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተናጠል ለማከናወን እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ እንደሚያሳስባቸውም አልሸሸጉም፡፡
ሆኖም በቀጣይ በሚደረጉ ድርድሮች ለጋራ መፍትሄ ከስምምነት እንደሚደረስ ያላቸው ተስፋ ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ያሉ ወንድሞቻችን በቀጣዩ የድርድር ወቅት ከስምምነት ለመድረስ በጎ ምላሽ ይኖራቸዋል የሚል ተስፋ አለኝ” ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስቀመጡት፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በተራዘመ የዲፕሎማሲ ድርድር ምክንያት እስካሁን መፍትሄ ያልተበጀለት አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ኢትዮጵያ ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ትፈልጋለች፡፡ ይህንንም በቅርቡ የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር ለሆነችው ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልዑካን ጭምር ገልጻለች፡፡ ሱዳን እና ግብጽም ይኸው ፍላጎት አላቸው፡፡ ሆኖም የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሃገራትን ጣልቃ ገብነት ይሻሉ፡፡