ሰአሊ አቡየ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ስእሎቹን በየመንገዱ እና ጋለሪ ላላቸው ሰዎች እየሸጠ ኑሮውን እየገፋ መሆኑን ይናገራል
ኢትዮጵያ በርካታ የስዕል ጥበብ ክህሎት ያላቸው በዚህም በዓለም አቀፍ መድረክ ሳይቀር አንቱታን ያተረፉ ሰዓሊያን ያፈራች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡
ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ እስክንድር ሞገስ፣ ዘርይሁን የትም ጌታ፣ወርቁ ጎሹ፣ወርቁ ማሞ፣ወሰኔ ኮስሮፍ፣ፕ/ር አቻምየለህ ደበላ፣ ጥበበ ተርፋ እንዲሁም ከዘመኑ ኤልያስ ሰሜን የመሰሉ አንጋፋ የስነ-ጥበብ ሰዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሰዓሊያኑ ከየዘመናቱ “የአሳሳል ፈሊጦች” እና ከዓለም የስነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ጋር ራሳቸው እያዛመወዱ እኩል ይራመዱ እንደነበርም ይነገራል፡፡
“ኤክስፕሬሽኒዝም፣ኢምፕሬሽኒዝም እና ኢንድቪዥዋሊስቲክ” ትልቅ ተጽእኖ የፈጠሩና የዓለም ንግግር ያላቸው የአሳሳል ፈሊጦች ኢትዮጵያውያኖቹ ሰዓሊያን ከሚታወቁባቸው የአሳሳል ፈሊጦች ናቸው፡፡
ነገርግን በኢትዮጵያ ውስጥ አንቱታን ያተረፉ ሰዓሊያን በሙያቸው ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ የሄዱበት የህይወት ጉዞ እጅጉን ግን የተለያየ ነው፡፡
ነገሮች ተመቻችተውላቸውና እድል አግኝተው ያላቸውን የጥበብ ክህሎት ለተደራሲያን ለመድረስ የቻሉ ሰዓሊያን እንዳሉ ሁላ፤ በችግር ምክንያት ያላቸውን የስነ-ጥበብ ክህሎት ወደ ገበያ ለማውጣትና ሀገራቸውን ለማስጠራት ያልቻሉ እድል ያላገኙም በዚያው ልክ በርካቶች ናቸው፡፡
ሰዓሊ አቡየ ወርቁ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ስዕል መሳልን ህይወቱ አድርጎ የኖረ ነገር ግን በችግር እየተፈተነ የሚገኝ ባለተሰጥኦ ሰዓሊ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከሰአሊ አቡየ ወርቁ ጋር አዲስ አበባ ከተማ(የካ አባዶ) ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መሄድ ቃል ምልልስ አድርጓል፡፡
ትውልድና እድገቱ አርሲ አቦምሳ እንደሆነ የሚናገረው ሰአሊ አበበ፤ በትውልድ ቦታው የነበሩት ጓደኞቹ የስእል ዝንባሌ ስለነበራቸው፤የእነሱ ዝንባሌ ስእል እንዲጀምሮ ተጽእኖ እንዳሳደሩበት ይናገራል፡፡
“ከልጅነቴ ጀምሮ ያየሁትን ስዕል መሳል እና በየሄድኩበት መሞነጫጨር አዘወትር ነበር” የሚለው ሰዓሊ አቡየ፤ እድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ በደርግ ዘመን ወደ ውትድርናው ዓለም ቢቀላቀልም የስዕል ፍቅሩ እንዳልተለየውና ከወታደር ቤት ሲመለስ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ሁለ ነገሩ ለጥበብ ሰጥቶ ህይወትን እየገፋ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ስዕልን መኖርያው ለማድረግ በማሰብ ኑረውን በአዋሽ-ሰባት የጀመረው አቡየ፤ ከሰባት ዓመታት የአዋሽ ሰባት ቆይታ በኋላ የሰዎችን ምክር ታክሎበት የጥበብ ስራዎቹን ለተደራሲያን ለማቅረብና የተሻለ ገቢ ለማግኘት በሚል በ2000 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገረው አቡየ ወርቁ፤ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ነገሮች እንዳሰባቸው ባይሆንም እንኳ የስዕል ስራዎቹን መተዳደሪያው አድርጎ እየኖረ መሆኑን ገልጿል፡፡
“አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ስዕሎቼን በየመንገዱ መሸጥ ጀመርኩኝ፤ አጥጋቢ ባይሆንም የስዕል ጋለሪ ላላቸው ሰዎች የስዕል ስራዎቼ እያቀረብኩኝ ህይወት ለመግፋት እየተንቀሳቀስኩኝ እኖራለው”ም ብለዋል፡፡
አቡየ የሚስላቸው በርካታ ስዕሎቹ “በፍየል ቆዳ ላይ ካለ ምንም የቀለም ቅብ የተሳሉ” መሆናቸው ብዙም ያልተለመደ የአሳሳል ቴክኒክ መሆኑ አል-ዐይን ኒውስ ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል፡፡
አቡየ በቆዳ ላይ ከሳላቸው ስዕሎች የበርካታ ዓለም አቀፍ መሪዎቸና የኢትዮጵያ መሪዎች ምስል እንዲሁም ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስዕሎች ይጠቀሳሉ፡፡
አቡየ ወርቁ በፍየል ቆዳ ላይ ስለተሳሉት ድንቅ ስራዎቹና የተጠቀመው የአሳሳል ቴክኒክን በተመለከተ ከአል-ዐይን ኒውስ ለቀረበለት ጥያቄም የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
“አዎ ለየት ያለ ነገር ነው ይዤ የመጣሁት፡ እርግጥ መጀመሪያ ስዕል ስጀምር ቆዳውን ከፋቅኩ በኋላ የቀለም ቅብ እጠቀም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ዶ/ር ለማ ጉያ አድናቂ ነኝ፤ የስዕል ፍቅሬ እያደገ ሲመጣ ሃሳቡ የወሰድኩትም ከእሳቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግን ድንገት ቆዳ ስፍቅ የተለየ ነገር ተመለከትኩኝ፤ የተፋቀው ራሱ ምንም ቀለም ሳይጨመርበት የሚያምር ሆኖ አየሁት፡፡ ከዛ በኋላ ምንም ቀለም ሳልጠቀም በተፈጥሮአዊ ቆዳ ብቻ መስራት እንደምችል አመንኩኝ” ሲልም ሁኔታውን ያስታውሳል፡፡
ሰዓሊ አቡየ ወርቁ ያለውን የጥበብ ተሰጥኦ ተጠቅሞ ስራዎቹ ወደ ገበያ ለማቅረብ የቻለንው ሁሉ እያደረገ ቢሆንም፤ ህይወት ከእጅ ወደ አፍ ብቻ በመሆኑ ያለውን አቅም በበለጠ በጥበብ ስራዎቹ ለማሳየት ድጋፍ እንደሚሻ ተናግሯል፡፡
አቡየ “አሁን ያለኝ ህይወት ከእጅ ወደ አፍ በሚባል ደረጃ ነው፤ እድሉን ባገኝ የጥበብ ስራዎቼን ማሳደግ እፈልጋለሁ፡፡ በተለይም መስሪያ ቦታ ባገኝ ስዕሎቼን በጥራትን በብዛት ማቅረብ እችላለሁ፤ አሁን ሁሉን ነገር የምሰራው ባያቿት ጠባብ ቤት ነው፡፡ መኖሪያየም መስሪያ ቦታየም ያቺ ጠባቧ ቤት ናት፡፡ እሷም በእድል ያገኘኋት ቤት ናት፤ ቆዳ ካለህ አከራይም ሆነ ጎረቤት አይፈልግህም፤ ስራው የሚረዳው ጥቂት ሰው ብቻ ስለሆነ፤ እናም ድጋፍ ባገኝ ደስ ይለኛል” ሲል ይጠይቃል፡፡