ጥንታዊው “የፓን አፍሪካኒዝም የጥበብ ት/ቤት በኢትዮጵያ”- አለፈለገ ሰላም
አጼ ኃይለ ስላሴ ለእይታዊ ጥበብ (Visual Art) ልዩ እይታ እንደነበራቸውና ለ‘አለ’ መመስረት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል
አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት በአፍሪካ የመጀመሪያውና “ጥንታዊው የፓን አፍሪካኒዝም የጥበብ ት/ቤት” በሚል ይታወቃል
በኢትዮጵያ የስነ-ጥበብ ትምህርት በሃሳብ ደረጃ ከተጸነሰ ዘመናት እንዳስቆጠረና ቀደም ባሉ ጊዜያት ተምረዋል በሚባሉ ሰዎች ልቦና ውስጥ የነበረ መሆኑን የታሪከ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
በንጉሥ ምኒልክ ዘመን ማብቂያና በዘውዲቱ የንግስና ዘመናት የነበሩ፤ ወደ ጣልያን እና ፈረንሳይ ተጉዘው ስዕል፣ ቀለም ቅብ እና ኪነ ሃውልት የመማር እድል ያገኙ ዘርይሁን ዶሚኒክ፣ ጌታቸው ዳፈርሳ፣ አገኘሁ እንግዳ፣ አበበ ወ/ጊዮርጊስ እና አፈወርቅ ገ/እየሱስ የተባሉ ኢትዮጵያውያን በአውሮፓ ቆይታቸው፤ “ጥንታዊውና ኢትዮጵያዊው የስነ-ስዕል ጥበብ በዘመናዊ የስነ ጥበብ ትምህርት መታገዝ አለበት” የሚል ከፍ ያለ ቅናት ይዘው የመጡ ሰዓሊያን እንደነበሩም ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያውያኖቹ ሰዓሊያን ከአውሮፓ መልስ ባለተሰጥኦ ህጻነትን መልምለው በፍላጎት ማስተማር ጀምረውም ነበር፡፡ በዚህም የያነው ወቅት “በኢትዮጵያ ዘመናዊ ስነ-ጥበብ ትምህርት የተጀመረበት ጊዜ” ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
የስነ-ጥበብ ሰዎቹ በራሳቸው ተነሳሽት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም፤ የስነ-ጥበብ ትምህርት በተቋም ደረጃ እንዲደራጅ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት ግን “አለፈለገ ሰላም” ናቸው፡፡
አል-ዐይን ኒውስ በአፍሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ ስለሚነገርለትና በዓለም የጥበብ አፍቃርያን ዘንዳ “ጥንታዊው የፓን አፍሪካኒዝም የጥበብ ት/ቤት” በመባል ስለሚታወቀው የአሁኑ ‘አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት’ አመሰራረት፣ ያለፈባቸው ምዕራፎችና አሁናዊ ሁኔታን በማስመለከት ከተቋሙ ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት
አለፈለገ ሰላም በአንጋፋው የአሜሪካ ቺካጎ የጥበብ አካዳሚ (Chicago Academy For the Arts) የተማሩና ለስድስት ወራት ያክል በስፔን፣ፈረንሳይ እና ጣልያን በመሳሰሉ ሀገራት በ20ኛው ክ/ዘመን በጣም ስመጥር በሚባሉ የስነ-ጥበብ ማዕከላት የሚገኙ ኦሪጂናል ስራዎች የጎበኙ ፣ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ አለፈለገ በአውሮፓ ምድር የተመለከቱትን ነገር ከፍተኛ ቁጭት ፈጥሮባቸው በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በራሳቸው ተነሳሽነት፤ ትንሽ እርሾ ገንዘብ በማውጣትም ጭምር የዘመናዊ የስነ-ጥበብ ትምህርትን አስፈላጊነትን በተመለከተ ለንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ምክረሃሳብ አቅርበው፤ ምክረ-ሃሳባቸው ተቀባይነት አግኝቶ ሃምሌ 16/1950 ዓ.ም በንጉሡ የልደት ቀን “አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት” እንደተመሰረተ ያስረዳሉ፡፡
ከሁለት ወራት በኋላ መስከረም 1951 ዓ.ም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ባለ ተሰጥኦ ልጆችን በመመልመል ፉም፣ ዊንዲ ኪንደር እና ሀርቨር ሳይለር በተባሉ የውጭ ሀገር መምህራን ማስተማር እንደጀመረም አቶ አገኘሁ አንስተዋል፡፡
የመንግሰታት አስተዋጽኦ - በስነ-ጥበብ
መንግስታት በተቀያየሩባቸው ዘመናት ሁሉ የየዘመን አጀንዳዎች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበሩና ያሉ መንግስታት በስነ-ጥበብ ላይ የየራሳቸውን አሻራ አኑረው አልፈዋል፡፡
አቶ አገኘሁም ስለዚሁ ስለ መንግስታት የማይናቅ አስተዋጽኦ ያነሳሉ፡፡
“ንጉሡ የመመስረት እና ዘመናዊ የስነ-ጥበብ ትምህርት በማለማመዱ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ንጉሡ ከትምህርት ቤቱ ጋር ትልቅ ቁርኝት እና ለእይታዊ ጥበብ (ቪዥዋል አርት) ልዩ እይታ ነበራቸው፡፡ የ1966ቱ አብዮት ሊፈነዳ በሃምሌ 1965 ዓ.ም ተማሪዎች ሲመረቁ መጥተው አይተዋል” በማለትም ነበር ንጉሡ ለስነ ጥበብ የነበራቸው ፍቅር የሚገልጹት፡፡
አቶ አገኘሁ የደርግ ዘመንን ሲገልጹት “የኛ ሀገር ምሩቃን ወደ ሶሻሊስት ሀገራት በመሄድ፤ በትላልቆቹ የሩስያው ሌኒንግራድ የሥዕል አካዳሚ (Leningrad School of Painting) እና የጀርመኑ ድሬስደን የጥበብ አካዳሚ (Dresden Academy of Fine Arts) የስነ-ጥበብ አካዳሚዎች ተምረው፤ በዘርፉ ጣራ የሚባለው ማስተር ኦፍ ፋይን አርትስ (Terminal Degree) እንዲማሩ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህም ቀደም ሲል በውጭ ሀገራት ዜጎች ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ከአውሮፓ መልስ በራሳችን ሰው እንዲተኩ ያስቻለ ትልቅ ምእራፍ ነው”ብለዋል፡፡
በኢህአዴግ ዘመን የጥበብ ዘርፍ እንዲሁም የሀሳብ ትምህርት “ቸል የተባለበት” ዘመን ነበር የሚሉት አቶ አገኘሁ አዳነ፤ ከነ ብዙ ጉድለቱ “ለዘመናት በመዋቅር ችግር ሲንገላታ የነበረ ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተዋህዶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነት እንዲያድግ መደረጉ በኢህአዴግ ዘመን እንደ ስኬት” ሊነሳ የሚችል ትልቅ ስራ ስለመሆኑንም ነው የሚናገሩት፡፡
የአሳሳል ፈሊጥ
አቶ አገኘሁ ተቋሙ በጊዜ ሂደት እያደገ እንደመምጣቱ ሁላ “በአሳሳል ፈሊጥ ረገድ ከዓለም የስነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ጋር እኩል የሚራመዱ ትልቅ ለውጦች ማሳየት የቻለ” ነው ይላሉ፡፡
“ኤክስፕሬሽኒዝም፣ ኢምፕሬሽኒዝም እና ኢንድቪዥዋሊስቲክ ትልቅ ተጽእኖ የፈጠሩና የዓለም ንግግር ያላቸው የአሳሳል ፈሊጦች ናቸው”ም ነው ያሉት የአለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተሩ አቶ አገኘሁ አዳነ፡፡
የአለ አሁናዊ ሁኔታ
አለ የጥበብና ዲዛይን ት/ቤት አሁን ላይ በአምስት የመጀመርያ ዲግሪ ፕሮግራሞች (እስከ ፒ.ኤች.ዲ የሚደርስ ኢንተርዲሲፕሊነሪ ቪዥዋል አርት፣ ኪነ-ቅርጽ፣ የቀለም ቅብ፣ የህትመት ጥበባት እና ኢንዳስትሪያል ዲዛይን) እንዲሁም በሁለት የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞች (ፊልም ፕሮዳክሽን እና ፋይን አርት) የማስተማር አገልግሎት እንደሚሰጥ አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል፡፡
“በሁሉም ደረጃዎች 200 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል”ም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውን ተከትሎ ግቢውን መጎብኘታቸውን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከጉብኝቱ በኋላ “ለመጀመሪያ ጊዜ በእንጠጦ ፓርክ ትልቅ የስነ-ጥበብ ማዕከል አሰርተውልናል” ሲሉም ለአል-ዐይን ኒውስ ተናግረዋል፡፡
የስነ-ጥበብ ማእከሉ መከፈት ከማህበረስቡ ጋር ከመደበኛ የማስተማር ሂደቱ በተጨማሪ “ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ እንድንገናኝ እድል ይፈጥርልናል”ም ነው ዳይሬክተሩ ያሉት፡፡
አለ የስነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት እንደ ገ/ክርስቶስ ደስታ፣ እስክንድር ሞገስ፣ ዘርይሁን የትም ጌታ፣ ወርቁ ጎሹ፣ ወርቁ ማሞ፣ ወሰኔ ኮስሮፍ፣ ፕ/ር አቻምየለህ ደበላ፣ ጥበበ ተርፋ እንዲሁም ከዘመኑ ኤልያስ ስሜን የመሳሰሉ አንጋፋ የስነ-ጥበብ ሰዎችን ያፈራ ጥንታዊ የፓን አፍሪካኒዝም ጥበብ ት/ቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡