በወፍ-በረር፡ የኪነ ጥበባት አርበኛው ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ
አንጋፋው የቲያትር ባለሞያ ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በ84 ዓመታቸው ሕይወታቸው አልፏል
ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሰዓት የተሸለሙበት ወቅት ለቴያትር እንዲገዙ አድርጓቸዋል
ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ84 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላይ ትልቅ አሻራቸውን ያሳረፉት ረ/ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ የቲያትር መምህር፣ ጸሐፊ ተውኔት፣ አዘጋጅ እና ተርጓሚ ነበሩ።
ረ/ኘሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ሐረርጌ ውስጥ ልዩ ስሙ ጎሮ ጉቱ በሚባል አካባቢ በ1929 ዓ.ም. ነው የተወለዱት፡፡
ወላጆቻቸውበልጅነታቸው በሞት የተነጠቁት ረ/ኘሮፌሰር ተስፋዬ አዲስ አበባ በማቅናት ዘመድ ቤት በመቀመጥ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
የተፈሪ መኮንን ተማሪ በነበሩበት ወቅት እግር ኳስና ሌሎች ጨዋታዎችን ያዘወትሩ ነበር።
ለስነጥበብም ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው አርቲስቱ በተለይ የከበደሚካኤልን "የትንቢት ቀጠሮ" ተውኔት ይወዱ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡
በ1948 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገቡ፡፡
የፊልም ወይም የመድረክ ተዋናይ የመሆን ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም አጠቃላይ ጥበብ (ጄኔራል አርትስ) ‘ሜጀር’ (ዋና ዘርፍ) አድርገው የሕግ ትምህርት አጠኑ፡፡
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው ለሁለት ዓመታት ቆይተዋል፡፡
"የቴያትር ጥበብን በማጥናት በኢትዮጵያ ያለውን የቴያትር ባህል ለማሳደግ" በቆራጥነት የተነሱት አሜሪካ እያሉ እንደነበር ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ቴአያትር እንዲያጠኑ ሐሳቡን የጫሩባቸው ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴያትር ባሳዩበት ወቅት በአተዋወን ብቃታቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተደስተው ሰዓት በመሸለም "ቴያትር" እንዲያጠኑ ከነገሯቸው በኋላ ነው፡፡
ከአሜሪካ በ1954 ዓ.ም. ከተመለሱ በኋላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ቤት በመቀጠር የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ሥራ የሆነውን "የሾህ አክሊል"ን በማዘጋጀትና የዋና ገፀባህሪውን በመወከል ተውነዋል፡፡
"የሺ" የሚል ተውኔት በመጻፍም ለመድረክ አብቅተዋል፡፡
በ1953 ዓ.ም. በእንግሊዝኛ ቋንቋ "ላቀችና ማሰሮዋ" የሚል ተውኔት ደርሰዋል፡፡
በርካታ ተውኔቶች ላይ የትወና ችሎታቸውን ያስመሰከሩ አጫጭር ልቦለዶችና ግጥሞቻቸው በሩሲያ ቋንቋ ተተርጉመው ሩሲያ ውስጥ ታትመዋል፡፡
የኡመር አል ኸያምን መጽሐፍ "ሩብ አያት" በማለት ተርጉመው አሳትመዋል፡፡ በተጨማሪም በ1965 ዓ.ም. መተከዣ የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡
ከደራሲው ስራዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ
1. መተከዣ (ግጥምና ቅኔ)
2. ጥላሁን ግዛው (ተውኔት)
3. ዕቃው (ተውኔት)
4. የሺ (ተውኔት)
5. አባትና ልጆች (ተውኔት)
6. ላቀችና ደስታ (ተውኔት)
7. ተሐድሶ (ተውኔት)
8. መተከዣ (ልብወለድ)
9. ዑመር ኸያም ልቦለዳዊ የሕይወት ታሪኩና ሩብአያቶቹ
( ትርጉም)
10. የመጨረሽታ መጀመርታ
የዘርፈ-ብዙ ጥበቦች ባለተሰጥኦው አንጋፋው አርቲስት ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ በበርካታ ፊልሞች እና ተከታታይ ድራማዎችም ላይ የጥበብ ብቃታቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡ የሼክስፒር ድርሰት የሆነውን ሀምሌት ቲያትርን ጨምሮ በበርካታ ቲያትሮች ላይም በድርሰት፣ በትወና እና በአዘጋጅነት ተሳትፈዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ጥበብ መምህር የነበሩት አርቲስቱ በመምህርነታቸው ብሎም በስራ ልምዳቸው በርካታ ጠቢባንንም አፍርተዋል፡፡
የኢትዮዽያ ደራሲያን ማህበር ለሚሊኒየም ካሳተመው አጀንዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስለ አርቲስቱ ያወጣውን ጽሁፍ በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡