ጥበብ አሳሹ ጥበበኛ፡ዮሴፍ ሰቦቅሳ ሰናይት
“የውስጣዊ ስሜቱንና እሳቤውን ምንነት በኢ-እውነታ የጥበብ ዘይቤ ያለገደብ ለመግለጽ አመቺ ኹኔታዎችን አገኘ …በሞቃትና ቀዝቀዛ ሕብረ ቀለማት በማነጻጸር ይጠይቅ ይመራመር ይፈልግና ያስስ ገባ”
“የምሰራበት የስነ ጥበብ ርዕስ ፍለጋ ነው፤ ወደፊትም የምሰራው በዚሁ ውስጥ ነው፡፡ ፍለጋ መፈለግ፣ማሰስ የሚል ትርጓሜ አለው”
“የምሰራበት የስነ ጥበብ ርዕስ ፍለጋ ነው፤ ወደፊትም የምሰራው በዚሁ ውስጥ ነው፡፡ ፍለጋ መፈለግ፣ማሰስ የሚል ትርጓሜ አለው”
ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ የህይወት ገጾች የሚቀዱ የጥበብ ቱርፋቶች በብሩሾቻቸው ለማበርከት ከሚታትሩ ተስፈኛ ወጣት ጥበበኞች መካከልም ይጠቀሳል፡፡ ወጣቱ ኪነ-ቀለመኛ (Painter) ዮሴፍ ሰቦቅሳ ሰናይት፡፡ ይህ ወጣት “ጥበብን አሳሽ ጥበበኛ” ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡ አብራችሁን ዝለቁ፡፡
ስነ ጥበባዊ የህይወት ጥሪ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብቶ እስከመማር ያደረሰው ዮሴፍ ከልጅነት እድሜ ዘመኑ ጀምሮ ከስነ ጥበብ ተወዳጅቷል፤ ከእምቦቃቅላ ለጋ የእድሜ ዘመኑ ጀምሮም ስዕልን ስሏል፡፡ ነፍስ አውቆ መሳል እስከጀመረበት ጊዜ ድረስም ዘጠኝ ያህል አመታትን በትምህርት አሳልፏል፡፡ ለዚህም አሁን በህይወት የሌሉት ወላጅ እናቱ ወ/ሮ ሰናይት የጎላ አበርክቶ ነበራቸው፡፡ ይህን አበርክቷቸውን በመታሰቢያነት ለመዘከርም የጥበብ ስራዎቹን መጠሪያ “ዮሴፍ ሰቦቅሳ ሰናይት”ሲል በእሳቸው ስም አድርጓል፡፡
“በሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል (ፑሽኪን) ሶስት አመት ፤ በአቢሲኒያ የስነጥበብ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሁለት ዓመት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ደግሞ አራት ያህል ዓመታትን ተምሬያለሁ፡፡ ነፍስ አውቄ መሳል እስከጀመርኩበት ጊዜ ድረስ የተለያዩ ስራዎችን ስሰራ ዘጠኝ ያህል አመታትን በትምህርት አሳልፌያለሁ ማለት ነው፡፡” ሲልም ያስቀምጣል፡፡
ልምድን ከትምህርት ጋር አገናኝቼ አሁን ካለሁበት ደረጃ ደረስኩ የሚለው ዮሴፍ የህይወትን አንዳች ገጽ በብሩሾቹ ክሱት ለማድረግ በምናቡ ዓለም ይማስናል፡፡ ስሜቱን ለመግለጽ እና አንድ አዲስ ነገርን ለመፍጠር የሚያስችሉትን የህይወትን ጓዳ ጎድጓዳዎችም ይነካካል፡፡ ቀለምን ከቀለም፤ ቀለምን ከከሰል፤ ከሰልን ከከሰል ያዋህዳል፤ ያደባልቃል፤ ያቀላቅላል የምናቡ ምጥ እስከሚወለድ ድረስ ሲጠበብ በሚውል በሚያድርበት የግል የመሳያ ስፍራው (ስቱዲዮ) ያሳልፋልም፡፡ የተከማቹ የምናብ ውጤቶቹም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
የዮሴፍ የስነ ጥበብ ቱርፋቶች የማህበረሰቡን የህይወት ጥጎች በማሰስ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ከፍ ያለ ትዕምርታዊ ዋጋ እና ትርጓሜ እንዳለው ከሚናገርለት እና በየማድቤቱ ከሚገኘው ምጣድ ማሰሻም ይቀዳሉ፡፡
የጥጥ ስሪት ካላቸው ለስላሳ ጨርቆች የሚዘጋጀው ማሰሻ ለብዙዎች የለሰለሰ የእለት እንጀራ መሰረት ነው የሚለው ዮሴፍ የስዕል ስራዎቹም ይህንኑ መነሻ አድርገው በአምስት ሂደቶች እንደሚቃኙና እንደሚያልፉ ይናገራል፡፡
“የምሰራበት የስነጥበብ ርዕስ ፍለጋ ነው፤ ወደፊትም የምሰራው በዚሁ ውስጥ ነው፡፡ ፍለጋ መፈለግ፣ማሰስ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ማሰስ የሚለው ደግሞ የስነ ጥበብ ህይወቴን የጀመርኩበት አንዱ ክፍል ነው፡፡ አምስት ሂደቶች አሉት፡፡ ማሰሻው የራሱን ሂደትና ቅኝቶች ይዞ አለ ፍለጋ ‘ሰርች’ አለ በፍለጋ ውስጥ ደግሞ የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለውን መስተጋብር አሳያለሁ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ያለው በስነጥበብ ውስጥ ያለ ነው፡፡ በማሰሻው እና በቴክኖሎጂው ከሰራኋቸው መካከል በቀለም ለይቼ የማወጣው ነው፡፡ ከዚያ ወደ ምናባዊ ማሰስ እገባና ቀለምና ከሰልን በመጠቀም ራሴ የማስበውን እሰራለሁ፡፡ እነዚህንም በስራዎቼ ውስጥ በደንብ አንጸባርቃለሁ፡፡”
ከምጣድ ላይ የሚነሳው የዮሴህ ፍለጋ አዲስ ነገር ማንሳት፤አዲስ ነገር ማግኘት፤ የነበረውን መያዝ፤ ያልሆነ ነገር ካለም መጣል ላይ ያተኩራል፡፡ ከዚያ እየተነሳም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በስራዎቹ ውስጥ ያንጸባርቃል፡፡ የዩኒቨርስቲ የመመረቂያ ስራውም በእነዚሁ የህይወት ፍልስፍናዎች የተቃኘ ነው፡፡
ዮሴፍ በሰው ልጅና በቴክኖሎጂ፤ በሰው ልጅ እና በሳይንስ መካከል ያለውን መስተጋብር እና ተሰናስሎ ለማወቅ አውቆም በጥበባዊ ስራዎቹ ህልው ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት የተመለከተው ታዋቂው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በባለፈው ዓመት ለ27ኛ ጊዜ የተካሄደውን የጋለሪያ ቶሞካ የስዕል ትርዒት አስመልክቶ በተዘጋጀው መጽሄት ላይ
“የውስጣዊ ስሜቱንና እሳቤውን ምንነት በኢ-እውነታ የጥበብ ዘይቤ ያለገደብ ለመግለጽ አመቺ ኹኔታዎችን አገኘ የሰው ልጅና ቴክኖሎጂን፤ቴክኖሎጂንና የሰው ልጅን በተምሳሌታዊ ምስላት አንዳንዴም በጥቁርና በነጭ ይበልጡን በሞቃትና ቀዝቀዛ ሕብረ ቀለማት በማነጻጸር ይጠይቅ ይመራመር ይፈልግና ያስስ ገባ” ሲል ስለ ወጣቱ ሰዓሊ የምስክርነት ቃሉን አስፍሯል፡፡
የህይወትን ዘርፈ ብዙ ትርጓሜዎች በብሩሹ ለማስቀረት የሚታትረው ዮሴፍ ትልቅ አበርክቶ አላቸው የሚላቸውን የማህበረሰቡን አሻራዎች በሞዛይክ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ጭምር ለማስቀረት የሚታታር ባለራዕይ ወጣት ነው፡፡ ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆንም በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች የሚገኙ የታሪክ አሻራዎችን በዚሁ የኪነጥበብ ዘርፍ ሰንዶ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ እስካሁንም የአቡነ ጴጥሮስን ኃውልት ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የታሪክ አሻራዎችን በሞዛይክ መልክ ሰርቶ ለሙዚዬም አብቅቷል፡፡
“ሞዛይክ ቅርስ የሆነ ትልቅ ስራ ነው፡፡ ልክ እንደ ሃገር ትልቅ አበርክቶ አለው፡፡ ስዕል ከስቱዲዮ ሲወጣ በህዝብ አደባባዮች ላይ ሲሰራ ማለትም ነው፡፡ [እኔም ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት] የአቡነ ጴጥሮስን ኃውልት ጨምሮ የስድስት ኪሎ የለግሃር ሃውልቶችን አዲስ አበባ ሙዚዬም ውስጥ የሚገኙ ጥሩ የሚባሉ የሞዛይክ ስራዎችንም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በመሆን ሰርቻለሁ፡፡”
ዐውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) ከህዝብ ጋር መገናኛ መንገድ ነው የሚለው ዮሴፍ ስራዎቹን በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ አቅርቧል፡፡ ከአስራ አምስት ባላነሱና በቡድን በሚዘጋጁ ዐውደ ርዕዮች ተሳትፏል፤ የራሱን ስራዎች በተናጠልም አቅርቧል፡፡
“ገና የአቢሲኒያ ተማሪ እያለሁ ነው ኤግዚቢሽን ማቅረብ የጀመርኩት፡፡ የቡድን ኤግዚቢሽኖችም ላይ ስሳተፍ ነበረ፡፡ ከ15 ያላነሱ ኤግዚቢሽኖችን ከፍቻለሁ በግል የከፈትኩትም አለ፡፡ በግሌ ሁለተኛውን በቅርቡ ለመክፈትም አስባለሁ፡፡”
ይህ መላው ዓለም እየተጨነቀ ያለበት የወረርሽኝ ወቅት ለኪነ ጥበቡም ያመቸ አይደለም፡፡ ለመሳል እንጂ በአዳራሽ ደግሶ ‘ኑ ስነ ጥበብን ተጋበዙልኝ’ ለማለትም አያስችልም፡፡ ረቂቅ የህይወት መልኮችን በስራዎቹ የማሳየት ህልም ያለው ወጣቱ ዮሴፍም “ለማምረት እንጂ ለማቅረብ ምቹ አይደለም” ባለው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ዘመኑ የወለዳቸውን የማህበረሰብ ትስስር ገጾች እንደ አማራጭ በመጠቀም ጥበብ ወዳዶችን ለመድረስ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡