ቀባሪ የሌላቸውን ሰዎች አፈር የሚያለብሰው የደሴው በጎ ፈቃደኛ "አብዱ ፋጤ"
አብዱ“የሰው ልጅ እንደሚሞት ቢያስብ ኑሮ ለመጨካከን ጊዜ ባልነበረው” ይላል
አብዱ ባለፉት 30 አመታት ውስጥ ከ4500 በላይ ቀባሪ የሌላቸውን ሰዎች ወግ እና ደምቡን ሳይለቅ አፈር አቅምሷል
አብዱ ከማል ረሺዲ ይባላል። ትውልድ እና እድገቱ በደሴ ከተማ ነው።
አብዱ እንደተናገረው ተለያዩ የበጎ አድርጎት ስራዎችን በገንዘብም ሆነ በጉልበት ከሚያግዙት ጥቃት ሰዎች ጋር በመሆን መስራት ችሏል።
በእድሜ በመግፋት፣ በድንገተኛ አደጋ እና በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው ያለፈ እና ቀባሪ የሌላቸው ሰዎችን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማድረግ የቀብር ስነስርአታቸውን በማስፈጸም ነው የሚታወቀው፡፡ አብዱ ባለፉት 30 አመታት ውስጥ ከ4500 በላይ ቀባሪ የሌላቸውን ሰዎች ወግ እና ደምቡን ሳይለቅ አፈር አቅምሷል።
ሙሉ ስሙ አብዱል ከማል ረሺድ ሲሆን የከተማው ሰዎች አብዱ ፋጤ ይሉታል። “ፋጤ” የሚለው መጠርያ አብዝቶ የሚወዳቸው የእናቱ ስም ሲሆን አሁን ላይ ብዙ ሰው የሚጠራውም በዚሁ ስያሜ ነው፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበረው ቆይታ የተወለድከው መቼ ነው? ተብሎ ሲጠየቅ “ምኑን አውቀዋለሁ ብለህ ነው፤ ከውልደቴ ይልቅ የምሞትበትን ቀን እያሰብኩ ለዛኛው አለም ስለምጠየቅበት መልካም ስራ ነው የማስበው። ግዴታ ነው ካልክ ግን በግምት 61 ሳልሻገር አልቀርም” ሲል መልሷል፡፡
በቤቱ ውስጥ ሁሌም ለቀብር ስነስርአት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን አሟልቶ በተጠራበት ቦታ ሁሉ ወንድ ፣ ሴት ፣ ክርስቲያን ፣ ሙስሊም ሳይል ሟቾች በተገቢው መንገድ አስክሬናቸው እንዲያርፍ በማድረግ 30 አመታትን አስቆጥሯል፡፡
ቃሬዛ (ስትሬቸር) ፣ መቆፈሪያ ፣ የአስክሬን ከፈኖች እና ለቀብር የሚያስፈልጉ ሌሎች ቁሳቁሶች ሁሌም በቤቱ ዝግጁ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡
አብዱ ይህን በጎ ተግባር የጀመረበትን አጋጣሚ ያስታውሳል።
ከዛሬ 30 አመት በፊት በደሴ መነሀሪያ ውስጥ በመኪና ረዳትነት የሚያገለግል ቤተሰብ የሌለው አንድ ልጅ መሞቱን ተከትሎ ጥሪ የደረሰው መዘጋጃ ቤት ልጁን ለመቀበር በመዘግየቱ አብዱ አስከሬኑን አጥቦ እና ገንዞ ከአካባቢው በተሰባሰበ ገንዘብ የቀብር ስነስርአቱ እንዲፈጸም አድርጓል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ቤተሰብ፣ እድር ወይም ቀባሪ የሌላቸው እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ለጉዞም ሆነ ለስራ ደሴ ከተማ ውስጥ መጥተው ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ሲኖሩ ቀድሞ የሚጠራው "አብዱ ፋጤ" ሆነ፡፡
“የሰው ልጅ ለመማር ራሱን የሚያዘጋጅ ከሆነ ህይወት ራሷ ትምህርት ቤት ናት። መልካምነት ከቤተሰብ እና ከአካባቢህ ትማራለህ፤ ዋናው ነገር አንተ የምትከተለው መንገድ ነው የሚወስነው፤ስራውን ስጀምር አጋጣሚ ነበር፤ ነገር ግን መጀመርያ እንደቀበርኩት ልጅ ያሉ ቤተሰብ እና ቀባሪ የሌላቸው ሰዎች እንዴት ይሆኑ ይሆን ብየ ማሰብ ጀመርኩ ከዛ ነው ስራየ ብየ የተያያዝኩት”፡፡
በጊዜ ሂደት የሚሰራውን በጎ ምግባር የሚመለከቱ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ሌሎች እሱን የሚያውቁት ሰዎች የቀብር ስነስርአት የሚያስፈጽምባቸውን የተለያዩ መሳርያዎች አሟሉለት፡፡
ቀጥሎም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የደሴ ከተማ ተወላጆች በወር እና በተለያየ ጊዜ በሚሰጡት ገንዘብ የአስከሬን መከፈኛ ጨርቆችን እና ሌሎች አላቂ እቃዎችን በማሟላት ዛሬ ላይ ሙሉ ጊዜውን ለዚህ በጎ አድርጎት ስራ አውሎት ይገኛል፡፡
አብዱ ይህን በጎ ስራ ይህን ያህል አመት ያለመሰልቸት እንዴት እንዳከናወነ ለጠየቅነው ጥያቄ፦
“እውነቴን ነው የምልህ ስራው በጣም አድካሚ እና ሰዎች አዘውትረው ሊሰሩት የሚችሉት አይደለም፤ ነገር ግን ሜቴን አሳምርልኝ እና ቀባሪ አታሳጣኝ በሚል ማህበረሰብብ ውስጥ አይደለም ብቸኛ ሆነህ በዘመድ ተከበህ ራሱ ምን ያህል ከባድ ነገር እንደሆነ ታውቀዋለህ፤ ዛሬ ላይ እድሜያቸው የገፋ በአልጋ ላይ የዋሉ የሞታቸውን ቀን የሚጠብቁ እና ቀባሪ የሌላቸው ሰዎች በየቤቱ ሞልተዋል። ህመምን ከመታመም እና የሞትን ቀን ከመቁጠር ባለፈ ደግሞ እዚህ ባዶ ቤት ሞቼ ብገኝ ማን ይሆን አንስቶ የሚቀብረኝ በሚል የሚጨነቁ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳይመስልህ፤ ቢያንስ የእነርሱን ጭንቀት መቅረፍ ችያለሁ ብየ አስባለሁ በዚህ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነኝ” ፡፡
በደሴ ከተማ በስራው ያተረፈውን ዝና ተከትሎ ቀባሪ ከሌላቸው ሰዎች “አብዱ ይቅበረኝ” የሚል ኑዛዜ ጭምር እንደሚደርሰው ይናገራል፡፡
ሟቾች እንደነገሩ አፈር እንዲቀምሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንደየ እምነታቸው አስፈላጊውን ሀይማኖታዊ ስርአት በማከናወን በየቤተ እምነታቸው መካነ መቃብር እንዲያርፉ ያደርጋል፡፡
አብዱ ለሶስት አስርተ አመታት ይህን ስራ ሲያከናውን የሟቾችን ስም ፣ የሞቱበትን ቀን ፣ አድራሻ እና የቀበረበትን ቦታ ሁሉ በስነስርአት መዝግቦ ያኖራል፡፡
ይህን የሚደርገው ደግሞ በአጋጣሚ የሟች ቤተሰቦች ቢገኙ እና ሟቹን ወደ ሌላ ቦታ ወስደው ማሳርፍ ቢፈልጉ በሚል ነው፡፡
በቀን ከአንድ ሰው በላይ የቀብር ስነስርአት እንደሚያስፈጽም የሚናገረው አብዱ በአደጋ እና ድንገተኛ ሁኔታ የሞቱ ሰዎች ሲያጋጥሙ ለፖሊስ በማሳወቅ አስፈላጊውን ምርመራ እና ማጣራት እንዲደረግ ሪፖርት ያደርጋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከእርሱ ጋር የቀብር ስራውን የሚያግዙ አስር በጎ ፈቃደኞች አብረውት ይሰራሉ። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ስላጋጠመው የተለየ አጋጣሚ ሲናገር፤ በአንድ ወቅት የቀብር ጉድጓድ እየቆፈረ ባለበት ለረጅም ጊዜ የተቀበረ የጥይት ሳጥን ፈንድቶ እርሱ እና አብረውት የሚሰሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ለአንድ ወር ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው እንደነበር ያስታውሳል፡፡
አብዱ ፋጤ የበጎ አድራጎት ስራውን እያሳደገ መጥቶ ከቀብር ስነስርአት ማስፈጸም ባለፈ በየቤቱ ቤተሰብ እና አስታማሚ የሌላቸውን በጽኑ የታመሙ ሰዎች ማስታመም እና መንከባከብ ፣ አርብ አርብ ደግሞ በሆስፒታሎች ውስጥ ጠያቂ የሌላቸውን ታማሚዎች መጠየቅ እና በተቻለ መጠንም የምግብ እና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አጫውቶናል፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ በመጨረሻ የጠየቅነው ጥያቄ ሞትን ትፈራለህ? የሚል ነበር።
“ሞት ምኑ ያስፈራል ብለህ ነው፤ የማይቀርን ነገር ለምን ትፈራለህ ዋናው ነገር ሀይማኖተኛ ከሆንክ ፈጣሪየ ፊት ስቀርብ የምናገረው በጎ ምግባር አለኝ ውይ ብለህ መዘጋጀት ነው፡፡
እኔ ቤት መጥተህ ብታይ መከፈኛ ጨርቅ ተንተርሼ ነው የምተኛው። መጥፎ ሰርተህ ሱፍ ከመልበስ በጎ አድርገህ ጆንያ መልበስ ይሻላል፡፡
ይህ የምታየው መጨካከን ሁሉ የመጣው ፍቅር ከማጣት እና ከስግብግብነት ይመስለኛል፤ እኔ ይህን ስራ ስሰራ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ የሚረዱኝ ሰዎች መልካም ስራየን ስላዩ ነው። ይህ በጎ ስራ እንደሚጋባ ያሳይሃል፡፡ የሰው ልጅ መሞቱን ቢያስብ ለመጨካከን ጊዜ ባልነበረው ነበር”፡፡
ይህን የበጎ አድራጎት ስራ ወደ ማህበር በመቀየር ተቋማዊ ቅርጽ የማስያዝ ህልም እንዳለው የሚገልጸው አብዱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ቦታ በመወሰድ የአረጋውያን ማቆያ እና መንከባከቢያ ድርጅት የማቋቋም ህልም ሰንቋል፡፡