“እዚህ የተገኝሁት በዚህ መድረክ በሀገሬ ላይ ለተቃጣው ያልተገባ ወቀሳ ምላሽ ለመስጠት ነው” - ቤኒያሚን ኔታንያሁ
ኔታንያሁ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር አድርገዋል
ኔታንያሁ የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት የኢራን ክፍል የለም፤ ይህ የመካከለኛው ምስራቅ እውነት ነው” ሲሉ ዝተዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ስሜት የተሞላበት ንግግር አድርገዋል፡፡
“ዘንድሮ በጉባኤው የመሳተፍ እቅድ አልነበረኝም፤ ሀገሬ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ እዚህ የተገኘሁት በመድረኩ ከተለያዩ አካላት ለቀረበብን ወቀሳ ምላሽ ለመስጠት ነው” በሚል ንግራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ እየተዋጋን ያለነው ከምድረ ገጽ ሊያጠፉን ከሚሹ “አረመኔ ጠላቶች” ጋር ነው ብለዋል።
“እስራኤል ኢራን በከፈተችው 7 አውደ ውግያዎች እየተዋጋች ትገኛለች፤ ተሄራን ከምታሰማራቸው ርህራሄ የለሽ ገዳዮች እራሳችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን፡፡ ይህ ሲሆን በኢራን ውስጥ የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት ቦታ አለመኖሩ ሊታሰብበት ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ቀን ማግስት ጀምሮ እስካሁን ከሄዝቦላ ከ8ሺህ በላይ ሮኬቶች እንደተተኮሱ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሉአላዊነታችንን ለመከላከል እያደረግን የምንገኘውን ውግያ ማንኛውም የዚህ ድርጅት አባል በእስራኤል የደረሰው ጥቃት ቢደርስበት የሚያደርገው ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በጉባኤው በእስራኤል ላይ ጠንካራ ትችት የሰነዘሩ ሀገራትን ወቅሰዋል፡፡
የጋዛው ጦርነት የሚጠናቀቀው ሀማስ የጦር መሳርያውን አስቀምጦ እጁን ሲሰጥ እንዲሁም ታጋቾችን ሲመልስ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን ይህ የማይሆን ከሆነ እስራኤል ሙሉ ለሙሉ አሸናፊነቷን እስከምታረጋግጥ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከ40 ሺህ የሀማስ ታጣቂዎች መካከል ግማሽ ያህሉ መማረካቸውን እና መገደላቸውን እንዲሁም የቡድኑ 90 በመቶ ሮኬቶች መውደማቸውንተናግረዋል፡፡
በእስራኤል እና ሳኡዲ አረብያ መካከል እርቅ ለመፍጠር እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነቶችን ለመጀመር ተቃርበን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሂደቱን ያስቆመው የጥቅምት ሰባቱ ጥቃት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢራንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ቴሄራን የኒዩክሌር ጦር መሳርያ ባለቤት እንዳትሆን እስራኤል አቅሟ የፈቀደውን በሙሉ እንደምታደርግ፤ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንዲጥል ጠይቀዋል፡፡
“ቴሄራን ለሚገኙ አምባገነኖች መልዕክት አለኝ ጥቃት የምትፈጽሙ ከሆነ ተመጣጣኝ ምላሽ እንሰጣለን። የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት የኢራን ክፍል የለም፤ ይህ የመካከለኛው ምስራቅ እውነት ነው” ሲሉ ዝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ባደረጉበት ወቅት በጭብጨባ ንግራቸውን ያጀቡ ተወካዮች እንዳሉ ሁሉ የኢራንን ጨምሮ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተወካዮች አዳራሹን ጥለው ሲወጡ ታይተዋል፡፡
የጋዛውን ትኩረት እያስለወጠ የሚገኘው የሄዝቦላህ እና የእስራኤል ውጥረት አሁንም ቀጥሏል፡፡
ከሰኞ ጀምሮ ቴልአቪቭ በሊባኖስ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች ወደ 800 የሚጠጉ ንጹሀን መገደላቸው እየተነገረ ይገኛል።