እስራኤል የአሜሪካ ቦምቦችን ተጠቅማ ቤሩትን እየደበደበች ነው ስትል ኢራን ከሰሰች
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ከኢራን ጋር እየተዋጋች መሆኗን ተናግረዋል
እስራኤል ከባለፈው ሰኞ እለት ጀምሮ ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ700 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
እስራኤል የአሜሪካ ቦምቦችን ተጠቅማ ቤሩትን እየደበደበች ነው ስትል ኢራን ከሰሰች።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ እስራኤል አሜሪካ ሰራሽ የሆኑትን በርካታ "በንከር በስተር" ቦምቦቸን በመጠቀም በትናንትናው እለት ቤሩትን ደብድባለች ሲሉ ከሰዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ "ዛሬ ጠዋት የእስራኤል አገዛዝ በአሜሪካ የተሰጡትን 5000 ፓውንድ ክብደት ያላቸውን በንከር በስተር ቦምቦችን ተጠቅሞ በቤሩት የመኖሪያ መንደሮችን ደብድቧል" ሲሉ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ ለተሰበሰበው የተመድ የጸጥታው ምክርቤት ተናግረዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በቤሩት ዳርቻ በሚገኘው የሄዝቦላ ዋና ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጥቃት የሰነዘረችው የቡድኑን ዋና አዛዥ ለመግደል ነበር። ነገርግን የቡድኑ መሪ የሆነው ሰኢድ ሀሰን ነስረላህ መገደሉን ለማረጋገጥ ጊዜው ገና መሆኑን ከፍተኛ የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
እስራኤል ከባለፈው ሰኞ እለት ጀምሮ ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ከ700 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በመቶሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤታቸው ተፈናቅለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በተካሄደው የተመድ 79ኛው ጠቅላላ ጉባኤ እስራኤል ከኢራን ጋር እየተዋጋች መሆኗን ተናግረዋል።
እየተዋጋን ያለነው ሊያጠፉን ከሚሹ “አረመኔ ጠላቶች ጋር ነው" ያሉት ኔታንያሁ “እስራኤል ኢራን በከፈተችው 7 አውደ ውግያዎች እየተዋጋች ትገኛለች፤ ተሄራን ከምታሰማራቸው ርህራሄ የለሽ ገዳዮች እራሳችንን መከላከላችንን እንቀጥላለን"ብለዋል።
ኔታንያሁ "በኢራን ውስጥ የእስራኤል ረጅም ክንድ የማይደርስበት ቦታ አለመኖሩ ሊታሰብበት ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሊባኖስ የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ጫና ቢደረግባትም፣ ከጋዛ ወደ ሊባኖስ ትኩረቷን ያደረገችው እስራኤል ተፈናቃዮችን መመለስን ጨምሮ ሁሉም ግቦቿ እስከሚሳኩ ድረስ ማጥቃቷን እንደምትገፋበት ገልጻለች።
የሊባኖስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደላ ቦሀቢቢ ግን ተኩስ አቁም መድረግ እንዳለበት አሳስበል። ሚኒስትሩ እንዳሉት ተኩስ አቁም የማይደረግ ከሆነ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ሰላም እና አለመረጋጋትን አደጋ ውስጥ የሚያስገባ አደገኛ ቅርቃር ሊፈጠር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ባለስልጣናት ለ21 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሀሳብ አቅርበዋል።