አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመቄዶንያ መስራች ቢኒያም በለጠ የክብር ዶክትሬት ሰጠ
“ሰውን ለመርዳር ሰው መሆን በቂ ነው” የሚል መርህ አንግቦ የተነሳው መቄዶንያ ለሺዎች መጠለያ ዋርካ ሆኗል
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአርቲስት ደበበ እሸቱም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሀገራቸውንና ወገናቸውን በቀናነት አገልግለዋል ላላቸው ሁለት ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
ዩኒቨርሲቲው ለመቄዶንያ በጐ አድራጎት ማህበር መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ እና ለአርቲስት ደበበ እሸቱ ነው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጠው።
አቶ ቢኒያም በሰው ልጆች ደህንነት ለሀገር የማይታካ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዩኒቨርሲቲው ዛሬ የክብር ዶክትሬቱን ሲያበረክትላቸው ገልጿል።
በታህሳስ 2002 ዓ.ም ከአሜሪካ ስደት ተመልሰው በቤተሰቦቻቸው መኖሪያ የጀመሩት በጎ ስራ በ2004 ወደ መቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከልነት አድጎ ባለፉት አስር አመታት አርአያ የሚሆን ተግባርን ፈጽመዋል።
40 ተረጂዎችን ይዞ ስራ የጀመረው ማዕከል በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ብቻ ከ7 ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ማረፊያ ሆኗል።
በክልል ከተሞችም ከ10 በላይ ቅርንጫፍ ማዕከላትን አቋቁሞ ጧሪ የሌላቸውን አዛውንቶች እና የአዕምሮ ህሙማን በቀን ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ይንከባከባል።
መቄዶንያ በአያት አካባቢ ከሶስት አመት በፊት በ3 ሺህ 600 ካሬ ሜትር ሥፍራ ባለ 15 ወለል የአረጋውያን መኖሪያ ሕንፃና ዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ መጀመሩ ይታወሳል።
በዚህ ህንጻ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ማስገባት የጀመረ ሲሆን፥ በርና መስኮቶችን ለመግጠምም በቅርቡ 1 ሚሊየን ዶላር በቀጥታ በዩቲዩብ ለመሰብሰብ የሚያስችል መርሃግብር መካሄዱ አይዘነጋም።
ህንጻው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በማዕከሉ እስከ 10 ሺህ ሰዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን፥ በቀጣይ ሶስት አመታትም ከጎዳና ላይ የሚነሱ ወገኖችን ቁጥር 20 ሺህ ለማድረስ ውጥን እንዳለው መቄዶንያ አስታውቋል።
“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የሚል መርህን አንግቦ የተነሳው መቄዶንያ መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ፥ ሁሉን ነገራቸውን ለወገናቸው በመስጠት ላከናወኑት አኩሪ ተግባርም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለአገር ትልቅ ውለታ ለዋለው አርቲስት ደበበ እሸቱም የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን በህይወት ካሉ አርቲስቶች ግንባር በግንባር ቀድምነት የሚነሳ ሲሆን፥ ለታሪክ የሚተላለፉ ድንቅ ስራዎችን ሰርቷል።
አርቲስት ደበበ መጀመሪያ በቴያትር የታየው በመንግስቱ ለማ በተጻፈው ያላቻ ጋብቻ ነው። “ጠልፎ በኪሴ”፣ “የአዛውንቶች ክበብ” እና “በቀይካባ ስውር ደባ” አዘጋጅቶ ከተወነባቸው ቲያትሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
“ኦቴሎ”ን ጨምሮ በርካታ የትርጉም ስራዎችን በማዘጋጀትና በመተወንም በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ አሻራውን አኑሯል።
ከመድረክና ፊልም ስራዎቹ ባሻገር ተማሪዎች የሚማሩባቸውን መጽሃፍትንም አበርክቷል።
ከአራት አስርት በላይ በኢትዮጵያ ቴያትር እና ፊልም እድገት ደማቅ አሻራውን ያኖረው አርቲስት ደበበ እሸቱ በተሰማራበት ዘርፍ ለሀገሩ እና ለወገኑ ላበረከተው አስተዋጽኦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ሃምሌ 13 2015 የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል።