ዩኒቨርሲቲው ለብጹዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የቆየዉን ተማሪዎች በዘሬው እለት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ዩኒቨርሲቲው ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉና ለብጹዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ማእረግ ሰጥቷል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ በሃይማኖት አባትነታቸው የተማሩትንና ያስተማሩትን በተግባር ለሚኖሩት፤ ሰውን በሰውነቱ ብቻ በማክበራቸው የክብር ዶክትሬት ማእረግ ሰጥቷል።
ኢንዲሁም ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በስፖርቱ ዓለም በማስጠራት ጀምራ ለኅብረተሰብ ፍቅርና አንድነት መጎልበት በመትጋቷ የዓመቱን የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
የክብር ዶክትሬት የተሰጣት የአትሌት ደራርቱ ቱሉ ስኬቶች በጥቂቱ
ከ50 ዓመት በፊት በአርሲ በቆጂ የተወለደችው ደራርቱ ቱሉ ለአፍሪካ ሴት አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ስፖርተኛ ናት።
በዓለም አቀፍ የስፖርቱ ማህበረሰብ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ንግስት በመባል የምትጠራው ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በፈረንጆቹ 1990 ላይ ቡልጋሪያ በተካሄደ የወጣቶች ውድድር ነበር።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተካሄዱ ውድድሮች ለሀገሯ 15 በላይ የወርቅ ብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎችን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለሀገሯ አስገኝታለች።
አትሌት ደራርቱ በነዚህ የአትሌቲክስ ድሎቿ እና በስፖርት አመራር ዘርፍ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የባህር ዳር ዩንቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷታል።
ዩንቨርሲቲው ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር ዶክትሬት ድግሪ የሰጣት በስፖርቱ ዘርፍ ለሀገሯ ላበረከተችው ታላቅ አስተዋጽዖ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው ገልጿል፡፡
ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ "ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በስፖርቱ ዓለም ያስጠራችና ለኅብረሰተብ ፍቅርና አንድነት መጎልበት የምትተጋ" መሆኗን ዩኒቨርሲቲው በሽልማቱ ወቅት ጠቅሷል።
ደራርቱ ቱሉ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገለች ትገኛለች።