አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) የክብር ዶክትሬት ተሰጣት
ሙዚቀኛ፣ የዜማና ግጥም ደራሲዋ ጂጂ ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ነው የአርት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የተሰጣት
ዩኒቨርሲቲው እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)ን ማክበር የኢትዮጵያን ታሪክና ኪነጥበብ ማክበር ነው ብሏል
አርቲስት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ከእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተበረከተላት።
የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በሴኔት ሌጅስሌሽን አንቀጽ ቁጥር 9/2010 መሰረት የአርት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰጣት በሙሉ ድምጽ ማፅደቁ ይታወቃል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው በዛሬው እለት ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ ለእጅጋየሁ ሽባባው የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
የአርቲስቷ ቤተሰቦችም የክብር ዶክትሬቱን ተቀለዋል።
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ቻግኒ ከተማ የተወለደችው እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) በኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደ ፈርጥ ከፈኩ የጥበብ ሰዎች ከቀዳሚዎቹ መካከል ተጠቃሽ ናት።
ሙዚቀኛ፣ የግጥምና ዜና ደራሲዋ ጂጂ የኢትዮጵያን ታሪክ፤ የዘመናት አኩሪ ታሪክ እና ድንግል ውበት በድንቅ ቋንቋና ለዛ ባላቸው ዜማዎቿ አቀንቅናለች።
ለዚህም “ኢትዮጵያ”፣ “አባይ”፣ “ካህኔ”፣ “ናፈቀኝ” የተሰኙት ስራዎቿ ጥቂት ማሳያ ናቸው።
“አድዋ” የተሰኘው ሙዚቃዋም የሰው ልጅ ክቡርነትን ለሀገር ከሚከፈል መስዋዕትነት ጋር አሰናስሎ የተሰራ ድንቅ ስራዋ ነው።
እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) የታላቁን ደራሲ የሀዲስ ዓለማየሁን ፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ መፅሐፍን መነሻ በማድረግ በአባ ዓለም ለምኔ ስም ውብ ቅላፄ ያለው ሙዚቃም ሰርታለች፡፡
ከሙዚቃ መምህሩ ከአለማየሁ ፋንታ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የተማረችው ጂጂ፥ ክራር፤ ማሲንቆ፣ ጊታርና ኪቦርድ መጫወት ትችላለች።
የጂጂ የሙዚቃ ስራዎች ለተለያዩ የሀገር ውስጥ እና አለማቀፍ ፊልሞችም ማጀቢያ ሆነው አገልግለዋል።
የእንጂባራ ዩኒቨርሲቲ ይህቺን የሀገር ምልክት ማክበር የኢትዮጵያን ታሪካ እና ባህል፣ ኪነጥበብ፣ ፍቅር አንድነትን ማክበር ነው ብሎም በዛሬው እለት የክብር ዶክትሬት ሰጥቷታል።