በኢትዮጵያ በግጭቶች ምክንያት 750 ሺህ ገደማ ህጻናት ከትምህርት ርቀዋል
750 ሺህ ገደማ ህጻናትን ወደ ትምህርት ለመመለስ የሚያስችል ዕቅድ ይፋ ሆነ
በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከትምህርት ርቀው የነበሩ 746 ሺህ ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ መርሃግብር ይፋ ሆነ፡፡
መርሃ ግብሩ “ኤዱኬሽን ካን ኖት ዌይት” በሚባል የተራድኦ ድርጅት ይፋ የተደረገ ሲሆን በአማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በ44 ወረዳዎች የሚተገበር ይሆናልም ተብሏል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የበላይነት ይመራል የተባለለት ይህ መርሃ ግብር በቀጣዮቹ ሶስት ተከታታይ ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ለስኬታማነቱ 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተመድቧል፡፡
እንደ ኢ.ዜ.አ ዘገባ ከሆነ ከተመደበው በጀት ውስጥ 27 ሚሊዮን ዶላሩ የተለቀቀ ሲሆን ቀሪው 138 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር በቀሪዎቹ ዓመታት ይለቀቃል፡፡
በዕቅዱ ይፋ ማድረጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዳይሬክተር ያስሚን ሸሪፍ፤ “መርሃ ግብሩ በጥቃት፣ በድርቅ፣ በመፈናቀልና በሌሎች ሁከቶች የተጎዱ ህጻናትን ተጠቃሚ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑ 746 ሺህ ህጻናት ውስጥ 365 ሺህ ሴቶች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ጺዮን ተክሉ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ ሁከቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ህጻናት መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተው የተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች ድጋፍ ጥራት ያለውን ትምህርት ለህጻናቱ ለማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋዎች የተነሣ 728 ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
“ኤዱኬሽን ካን ኖት ዌይት” በ30 ሃገራት ተመሳሳይ ተግባር ያከናውናል፡፡