በአልመክቱም ስታዲዬም በመካከለኛው ምስራቅ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መልእክት ያስተላልፋሉ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ1 ቀን በኋላ ዱባይ ናቸው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከየካቲት 5 እስከ 7 ለሚያደርጉት ጉብኝት እየተካሄደ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ውይይት ተካሄደ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከነገ በስቲያ ጀምሮ ለሶስት ቀን የሚቆይ ጉብኝት እንደሚደርጉ መገለፁ ይታወሳል።
በተለይ አርብ የካቲት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በዱባይ ከተማ ሸባብ አልአህሊ ክለብ በአልመክቱም ስታዲያም በመገኘት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና በመካከለኛው ምስራቅ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መልእክት ያስተላልፋሉ።
ይህንኑ ዝግጅት ለማስተባበር ከህብረተሰብ አደረጃጀቶች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከልማት ማህበራት የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።
ከሰባቱም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲቀበሉና እንዲገናኝ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ እንቅስቃሴዎች ፣ መስተንግዶ እና የሎጀስቲክ ስራዎች የስራ ሂደት በተመለከተ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት እና የአብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ በተገኙበት ውይይት መካሄዱን ከዱባይና ሰሜን ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ቆንስላ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመገናኘት ከየግዛቶቹ ወደ ዝግጅት ቦታው ለሚመጡ ዜጎች በየግዛቶቹ ከተሞች አማካይ ቦታዎች ነጻ የአውቶቡስ የትራንስፖርት አገልግሎት የተዘጋጀ ሲሆን፥ አውቶቡስ ማቆሚያ ቦታዎች እና አስተባባሪዎችን የተመለከተ መረጃዎች በቀጣይ ለህብረተሰቡ እንደሚገለፅ ተጠቁሟል።