ምርጫ ቦርድ ጃዋርን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠው የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን ጠየቀ
ምርጫ ቦርድ ጃዋርን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠው የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲን ጠየቀ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ/ም ለኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በጻፈው ደብዳቤ በቅርቡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስን (ኦፌኮ) የተቀላቀሉትን የአቶ ጃዋር መሃመድን ዜግነት አጣርቶ እንዲያሳውቀው ጠይቋል፡፡
ከአሁን ቀደም በጻፋቸው 2 ደብዳቤዎች ግለሰቡ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን መልሰው ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ እንዲያቀርብ ለፓርቲው ማስታወቁን የገለጸው ቦርዱ ግለሰቡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነና ዜግነታቸው እንዲመለስላቸው አመልክተው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማግኘታቸውን በመጠቆም ሰነድ መጠየቁ አግባብ እንዳይደለ የሚያስታውስ ምላሽ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን እና ከተጠቀሱት አንቀጾች አንጻር የፓርቲውን ምላሽ መርምሮ የመጨረሻ ያለውን ምላሽ ለመስጠት ቢችልም ውሳኔው የኤጀንሲውን ስልጣን ሊጣረስ እንደሚችል በመጠቆም ወደፊትም ሊመጡ ለሚችሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሆን በሚችል መልኩ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጠው ስለመጠየቁም ነው የገለጸው፡፡
በመሆኑም አንድ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣የሌላ ሃገር ዜግነት ያለውና መደበኛ ኑሮውን በኢትዮጵያ ያደረገ፣የሌላ ሃገር ዜግነቱን የተወ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ እንዲመለስለት ያመለከተ ካለ ኤጀንሲው ውሳኔ ዜግነቱን ወዲያውኑ መልሶ ማግኘት ይችል/አይችል እንደሆነና ከአሁን ቀደም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተሰጠ ውሳኔ ካለ እስከ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ/ም ድረስ በዝርዝር እንዲያሳውቀውና ማብራሪያውን እንዲልክለት በደብዳቤው ጠይቋል፡፡