የቤተሰብ አባላቱ አንድን ወንዝ በመሻገር ላይ ነበሩ ተብሏል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ነዋሪ የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት በድንገተኛ ጎርፍ አደጋ ህይወታቸው አለፈ፡፡
በጅሁር ንዑስ ወረዳ በዣትና ይቆሮ ቀበሌ ይዘኝ ጎጥ ይኖሩ ነበር የተባለላቸው የቤተሰብ አባላቱ ጎዴቤራ የተሰኘ የአካባቢውን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ በመጣ ድንገተኛ ጎርፍ መወሰዳቸውን የንዑስ ወረዳው መርማሪ ፖሊስ ሳጅን አቤል ብዙወርቅ ሙላቴ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ይህ የሆነው አርብ ሃምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 11፡30 ነው እንደ መርማሪ ፖሊሱ ገለጻ፡፡
በዕለቱ በአካባቢው ደጋማ ስፍራዎች ለአንድ ሰዓት እና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በርከት ያሉ ትናንሽ ገባሮች ያሉት ጎዴቤራ ወንዝ ሞልቶ ነበር ያሉት ሳጅን አቤል አባት፣ እናት እና ልጅ የሆኑት የ47 ዓመቱ አቶ ደምሳሽ ቦጋለ ፣የ40 ዓመቷ ወ/ሮ አየለች ዘዉዴ እና የ15 ዓመቷ ታዳጊ ልጃቸው ይጋርዱ ደምሳሹ ወንዙን ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት በመጣ ድንገተኛ ጎርፍ መወሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ ማንም ያያቸው ያልነበረውን የቤተሰብ አባላቱ አስከሬን ከአስቸጋሪ ፍለጋ በኋላ ትናንት እኩለ ቀን አካባቢ በወንዙ የተለያዩ አካባቢዎች መገኘቱን የገለጹት ሳጅን አቤል ስርዓተ ቀብራቸዉ ዛሬ እለተ እሁድ ነሃሴ 2 ቀን 2013 ዓ/ም ተፈጽሟልም ብለዋል፡፡
የቤተሰብ አባላቱ ዘመድ ለመጠየቅ ይሁን ለስራ በውል አላወቅሁትም ባሉት ጉዳይ ይገረኝ ወደሚባል የአካባቢው መንደር ሄደው እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡
ሆኖም መንገድ መጀመራቸውን ያውቅ የነበረው ቤተሰብ ሁኔታው አሳስቦት ገደል ገብተው አልያም በጎርፍ ተወስደው ሊሆን ይችላል በሚል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ባደረገው ፍለጋ የቤተሰብ አባላቱን አስከሬን ማግኘቱንም መርማሪው ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
አቶ ደምሳሽ ቦጋለ እና ወ/ሮ አየለች ዘዉዴ የ5 እና የ7 ዓመት የሆኑትን ጨምሮ አራት ቀሪ ልጆች እንዳሏቸውም ነው ሳጀን አቤል የገለጹት፡፡