በሱዳን በጣለ ከባድ ዝናብ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ ተጥለቀለቁ
“ከ800 በላይ ቤቶች ፈርሰዋል፤ 4 ሺ 400 ገደማ ቤቶች ደግሞ ተጎድተዋል”ም ነበር ተመድ በወቅቱ ያለው
ተመድ ከሰሞኑ ከሃገሪቱ 18 ክልሎች በ8ቱ የሚገኙ 12 ሺ ገደማ ሱዳናውያን በጎርፍ አደጋ መጠቃታቸውን ማስታወቁ የሚታወስ ነው
በሱዳን ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በሺወች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ መጥለቅለቃቸው ተነገረ፡፡
ካርቱም የሚገኘው የኤኤፍፒ ዘጋቢ የከተማይቱ ጎዳናዎች በጎርፉ መጥለቅለቃቸውን ዘግቧል፡፡
ክረምት በመጣ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ በሱዳን የተለመደ ነው፡፡
በሰሜን ምስራቃዊ ሱዳን የምትገኘው የአጥባራ ከተማ በተመሳሳይ መልኩ መጥለቅለቋን የሃገሪቱ ዜና አገልግሎት (ሱና) ዘግቧል፡፡
ከሃገሪቱ 18 ክልሎች በ8ቱ የሚገኙ 12 ሺ ገደማ ሱዳናውያን በጎርፍ አደጋ መጠቃታቸውን ባሳለፍነው ሃሙስ ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታዎች እንደሚያስፈልጉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
“ከ800 በላይ ቤቶች ፈርሰዋል፤ 4 ሺ 400 ገደማ ቤቶች ደግሞ ተጎድተዋል” ሲል ነበር ተመድ በወቅቱ ያስታወቀው፡፡
በሱዳን ባለፈው ዓመት 650 ሺ ዜጎች ለከፋ የጎርፍ አደጋ ተጋልጠውና 110 ሺ መኖሪያ ቤቶች ፈርሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎ ካርቱም ለ3 ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሱዳንን ከእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ለመጠበቅ ያስችላል መባሉም የሚታወስ ነው፡፡