ሱዳን የአባይ ወንዝ ፍስት መጠን ከፍ በማለቱ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል ስትል ዜጎቿን አስጠነቀቀች
የኢትዮጵያ ውሃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በሰከንድ 6 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ግድቡ እየደረሰ ነው ብለዋል
የሱዳን ውሃና መስኖ ሚኒስቴር የአባይ ወንዝ እለታዊ ፍስት መጠን ወደ 400 ሚሊዮን ኪዩቡክ ሜትር ከፍ ማለቱን አስታውቋል
የሱዳን ውሃ እና መስኖ ሚኒስቴር ባስተላለፈው የጥንቃቄ መልዕክት የናይል ወንዝ የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡ከዚህ በፊት የወንዙ አማካኝ እለታዊ የውሃ መጠን ከ100 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ወደ 400 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ከፍ ማለቱን ሚኒስቴሩ በድረገጹ አስታውቋል።
በመሆኑም ሱዳናዊያን በውሃ መጥለቅለቅ አደጋ እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሚኒስቴሩ የማስጠንቀቂያ መልዕክቱን አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ እየዘነበ ያለው የውሃ መጠን ለወንዙ ውሃ መጠን መጨመር በምክንያትነት ያስቀመጠው ተቋሙ በሮዛሪየስ፤ ሲንጋ፤ሴናር እና ዱምዳኒ የውሃ ማጠራቀሚያ ማዕከሎች ያለው የውሃ መጠን ከሳምንት ሳምንት እየጨመረ መሆኑንም ጠቅሷል።
በነገው ዕለትም የውሃ ፍሰቱ ተመሳሳይ ስለሚሆን የጀበል አውሊያ ግድብ ውሃ ሙሌት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
ቀሪዎቹ ግድቦች ማለትም ሜሮዌ ፤ሲታት እና አትባራዊ ግድቦች ውሃ መያዛቸውን ስለሚቀጥሉ እና በቅርቡ ስለሚሞሉ ዜጎች ህይወታቸውን እና ንብረቶቻቸውን ከጎርፉ እንዲጠብቁ ሲል አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ውሃ፤መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒሰትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየዘነበ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብም በሰከንድ 6 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የውሃ መጥለቅለቅ ሊያጋጥማቸው ይችላል ብለዋል።