ግጭቱ ከተከሰተ ጀምሮ እስካሁን ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ከተማ ድረስ ባሉ አከባቢዎች የመንግስት ተቋማና ባንኮች ዝግ መሆናቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል
በምስራቅ አማራ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት ላለፉት ስምንት ቀናት ተዘግቶ የነበረው የአዲስ አበባ-ደሴ መንገድ ዛሬ ጠዋት በመከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ተከፍቷል፡፡
ከስምንት ቀን በፊት የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ልዩ ቦታው አጣዬ ከተማ እና ዙሪያ ባሉ የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢዎች የተጀመረው ግጭት የበርካቶችን ህይወት ሲቀጥፍ እስካሁን ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት በአጣዬ፤ጀውሃ፤ካራቆሪ፤ማጀቴ፤ከሚሴ እና ሸዋሮቢት ግጭቱ የቆመ ቢሆንም አሁንም ነዋሪዎቹ ግጭቱ መልሶ ሊከሰት ይችላል፤በአካባቢው በቂ የጸጥታ ሃይል የለም ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።
በትናንትናው ዕለትም በኤፍራታና ግድም ወረዳ አላላ እና አሽኳይ ሸረፋ ቀበሌዎች ከአጎራባች የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ስር ካለው ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ቀበሌዎች በመጡ ታጣቂዎች መጠቃታቸውን እና ሰዎች መገደላቸውን ንብረታቸውም እንደወደመባቸው ተናግረዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የሚያስኬደው ዋናው መንገድ ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ከተማ ድረስ በመዘጋቱ የጸጥታ ስራውንም ሲያደናቅፍ እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ይሁንና ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በሀገር መከላከያ ሰራዊት አጃቢነት ሚኒባሶች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ ከፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰምተናል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ግጭቱ በተከሰተባቸው ከሸዋሮቢት እስከ ከሚሴ ከተማ ድረስ ባሉ አከባቢዎች የመንግስት ተቋማት፤ባንኮች እና ሌሎች የንግድ ድርጅቶች ዝግ ናቸው።
አል ዐይን ነዋሪዎቹ ስለአነሱት የደህንነት ስጋትና በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።