በአማራ ክልል አጣዬ አካባቢ በተከሰተ የጸጥታ ችግር በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ
በአካባቢው የፌዴራል ፖሊስ ቢሰማራም በቂ እንዳልሆነ ነው የተጠቆመው
ትናንት ምሽት የተጀመረው ተኩስ እስካሁን ድረስ እንዳልቆመ ተገልጿል
በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ነዋሪዎች በአጣዬና አካባቢው ትናንት ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ተኩስ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከዚህም በፊት በአካባቢው አልፎ አልፎ ተኩስ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ግን በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡
ከባድ የሆነ የተኩስ ልውውጥ በአካባቢው በመኖሩ ከቤታቸው መውጣት እንዳልቻሉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ የደረሰውን ጉዳት በውል ባያውቁትም የሰው ህይዎት መጥፋቱን አስክሬን ሲመጣ ማየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ባንኮችና የሰዎች ንብረት እንደተዘረፉም ነዋሪዎቹ መናገራቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡
ነዋሪዎቹ ዘግይቶም ቢሆን የፌደራል ፖሊስ መግባቱን ተናግረው የተኩስ ልውውጡ ግን አለመቆሙን ነው የጠቆሙት፡፡
የሰሜን ሽዋ ዞን የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ፣ ከመጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣየና አካባቢው እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች ተኩስ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡
ለግጭቱ መከሰት ምክንያቱ አጣዬ አካባቢ “አንድ ሰው በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል” የሚል መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ጉዳዩን አመራሩ በማወያየት በሽምግልና የተፈታ ቢሆንም ድንገት ትናንት ማታ ላይ ተኩስ መከፈቱን አብራርተዋል፡፡
ተኩሱ ከተጀመረ በኋላ የጸጥታ መዋቅሩን በማንቀሳቀስና የማረጋጋት ሥራ ሲሠራ ከቆየ በኋላ ወደ አካባቢው የፌደራል ፖሊስ እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል ብሏል አብመድ በዘገባው፡፡
ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑና ሊቆጣጠር የሚችል በቂ የጸጥታ ኃይል ባለመሠማራቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሰፍቶ ተኩሱ እስካሁን መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ተኩሱ በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡ አሁን ላይ ተኩሱ በመጠኑም ቢሆን ጋብ በማለቱ የማረጋጋትና ሌሎች ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ነው ኃላፊው የገለፁት፡፡
“አንዳንድ ቦታዎች ለእንቅስቃሴ የተዘጉ እና የተያዙ ቢሆንም” ባለው ኃይልም ቢሆን ችግሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል እንዲገባ ለመንግስት ጥያቄ መቅረቡንም አንስተዋል፡፡
በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ወደፊት ተጣርቶ ለሕዝብ እንደሚገለጽም ነው አቶ አበራ የተናገሩት፡፡