በአዲስ አበባ ከአደባባዮች ላይ የተነሱ ሐውልቶች የት ናቸው?
የካርል፣ ቦብ ማርሌ፣ ፑሽኪን፣ የሜክሲኮ ወዳጅነትና ሌሎችም ሐውልቶች ከአደባባይ ላይ ከተነሱት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ሐውልቶቹን ወደ አደባባይ ለመመለስ ጥረት ላይ መሆኑን ገልጿል
የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ብዙ መልኮች ያሏት ከተማ ነች። ከከተማዋ ውበቶች መካከል በየአደባባዮቿ ያሉት ሀውልቶች ዋነኞቹ ሲሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ሀውልቶችን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተክላለች።
ብዙዎቹ በየጊዜው እየታደሱ አሁንም ያሉ ቢሆንም በብዙ ምክንያቶች ከየአደባባዮች ላይ ተነስተው ወደ መካዝን የተላኩ ሐውልቶች አሉ።
ከነዚህ መካከልም በፈረንጆቹ 2002 ከሞስኮ ከተማ ለአዲስ አበባ የተበረከተው የደራሲ አልክሳንደር ሰርጌቪች ፑሽኪን ሐውልት፣ የጃማይካዊው የሬጌ ሙዚቀኛ ቦብ ማርሌ፣ የኦስትሪያዊ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው እና የሰዎች ለሰዎች ድርጅት መስራቹ ካርል ዋነኞቹ ናቸው።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በጣልያን የቅኝ ግዛት ወረራ በተፈጸመባት ወቅት እና የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት አጼ ሀይለስላሴ በተመድ ተገኝተው አቤቱታቸውን ባቀረቡበት ወቅት በብቸኝነት የኢትዮጵያ ደጋፊ የነበሩት የሜክሲኮ የተመድ ተወካይ ምስልን የያዘው የሜክሲኮ ወዳጅነት ሀውልትም ከአደባባዮች ላይ ከተነሱ ሐውልቶች መካከል ተጠቃሽናቸው።
ሐውልቶቹ በአደባባይ ላይ የተቀመጡት በየጊዜው በነበሩ የመንግስት አስተዳድር ውሳኔዎች እንደሆነ ቢገለጽም ሀውልቶቹ ሲነሱ በቅርቡ ወደቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ በሚል በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጹ ቆይተዋል።
አል ዐይን አማርኛ እነዚህ ሀውልቶች አሁን የት ናቸው ለምን ወደ ቀድሞ ቦታቸው አልተመለሱም ቀጣይ እጣ ፈንታቸውስ ምንድን ነው ሲል ለሀውልቶቹ ቅርበት ያላቸውን ግለሰቦች እና ተቋማትን አነጋግሯል።
በኢትዮጵያ 460 ትምህርት ቤቶችንና ስምንት የሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችን በመገንባት እና የብዙ ዜጎችን ህይወት በመቀየር የሚታወቁት የሰዎች ለሰዎች መስራቹ ካርል ሀይንስ በም በአዲስ አበባ ሐውልት ቆሞላቸው ነበር።
የኢትዮጵያ ለእኝህ ባለውለታ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በአዲስ አበባ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ አደባባይን በመሰየም ሐውልታቸው ተመርቆ በዚህ አደባባይ ላይ ተሰቅሎም ነበር።
ይሁንና ይህ ሐውልት ከስድስት ወር በፊት ድርጅታቸው በማያውቀው መንገድ አደባባዩ መፍረሱ እና ሐውልቱም መነሳቱን የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ይልማ ታዬ ለአልዐይን ተናግረዋል፡፡
የሐውልቱ መነሳትን እና አደባባዩ መፍረሱን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ይልማ የካርል ሐውልት በዚያው ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ሌላ ቦታ እየተዘጋጀለት መሆኑን ከከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን ጋር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አክለዋል።
እንደ አቶ ይልማ ገለጻ የካርል ሐውልት በቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ታከለ ኡማ የአስተዳድር ጊዜ ሊነሳ ተወስኖ የነበረ ሲሆን በተደረገ ውይይት ሐውልቱ ባለበት እንዲቀጥል ተወስኖ ነበር።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በበኩላቸው የካርል አደባባይ የፈረሰው የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ለማቅለል ታስቦ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም ብለዋል።
“ዶካተር ካርል ሄንዝ በም የኢትዮጵያ የክፉ ጊዜ ባለውለታ እና ለሀገር ብዙ ያበረከቱ ሰው መሆናቸውን የከተማው አስተዳደድር ያምናል“ ያሉት አቶ እያሱ፤ ሐውልቱ በዚያው አካባቢ ባለው ከብስራተ ገብርኤል ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሚወስደው መንገድ ላይ ለማስቀመጥ እሳቸው ከመሰረቱት ድርጅት አመራሮች ጋር ከስምምነት ላይ መደረሱንም ነግረውናል።
እንደ አቶ እያሱ ገለጻ ሐውልቱን በተሻለ ጥራት ከተማ አስተዳድሩ በራሱ ወጪ በማሰራት ላይ ሲሆን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ በተዘጋጀላቸው ልዋጭ ቦታ ላይ ይቀመጣል።
ሌላኛው ከአደባባዮች ላይ የተነሳው ሐውልት የኢትዮ-ሩሲያ ወዳጅነት መገለጫ እንደሆነ የሚገለጸው የደራሲ አልክሳንደር ሰርጌቪች ፑሽኪን ሐውልት ሲሆን ሐውልቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ተቀምጦ ይገኛል።
የሩሲያ መዲና ከሆነችው ሞስኮ ከተማ በስጦታ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠው ይህ ሐውልት ለምን ከአደባባይ ላይ ተነሳ ለምንስ ሌላ ቦታ አልተሰጠውም በሚል ላቀረብነው ጥያቄም አደባባዩ የፈረሰው በተመሳሳይ የትራፊክ መጨናነቅን ለማስቀረት መሆኑን አቶ እያሱ ጠቅሰዋል፡፡
አካባቢው አሁንም ፑሽኪን አደባባይ በሚል እየተጠራ ነው የሚሉት አቶ እያሱ ሐውልቱ ወደተዘጋጀለት አደባባይ እንዲመለስ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑንም ነግረውናል።
በ1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የሬጌ ሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደድር የቦብ ማርሌይ ሐውልትን ለማቆም እና አደባባይ በስሙ ለመሰየም ቃል ገብቶም ነበር።
ከተማዋ በዚህ ቃሏ መሰረትም ከመገናኛ ወደ ቦሌ ድልድይ በሚወስደው መንገድ አማካኝ ላይ በሚገኘው የገርጂ አምፔሪያል ማለፊያ መንገድ ላይ ከስድስት ዓመት በፊት የቦብ ማርሌይን ሐውልት እና አደባባዩም በስሙ ለመሰየም በቅቶ ነበር።
ይሁንና ሐውልቶ ከቆመ ከሁለት ዓመት በኋላ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሐውልቱም ሲነሳ አደባባዩም ሊፈርስ እንደቻለ የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን ገልጿል።
የቦብ ማርሌ ሐውልት አሰሪ ኮሚቴ መካከል ዋነኛው የሆኑት የሬጌ ሙዚቀኛው አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ እንዳሉን ከሆነ ሐውልቱ ከተነሳ አራት ዓመታት እንዳለፉት ነግረውናል።
የቦብ ማርሌ 60ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ባለቤቱ ሪታ ማርሌይ እና እና ሌሎች የፓን አፍሪካ ጽንሰ ሀሳብ አቀናቃኞች በተገኙበት አዲስ አበባ ከተማ የቦብን ሐውልት ለማቆም በወቅቱ አስተዳድር በኩል ቃል ገብታም ነበር ብለውናል ሙዚቀኛ ዘለቀ።
በዚህ መሰረት ሐውልቱን ዳግም አደባባይ ላይ ለማቆም ከከተማ አስተዳድድር ጋር በየጊዜው ውይይት ቢደረግም የከተማዋ አመራሮች ቶሎ ቶሎ መቀያየር ጉዳዩ እልባት እንዳያገኝ አድርጎታል ብሎናል።
“የተለያዩ ቦታዎችን ለከተማ አስተዳድሩ ጥቆማ ስንሰጥ ቆይተናል” ያሚሉት ሙዚቀኛ ዘለቀ “በቅርቡ ለጊዜው ስሙን መናገር በማልፈልገው ቦታ ላይ ሐውልቱ እንደሚቆም እምነት አለን” ሲሉም አክለዋል።
አሁን ላይ ከከተማ አስተዳድሩ ጋር የሚደረገው ውይይት እንዳለ ሆኖ ጉዳዩን ከፌደራል መንግስት በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ እና እንዲያግዝ እየተነጋገሩበት መሆኑን ሙዚቀኛ ዘለቀ ገሰሰ ገልጸዋል።