የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 100 ሺህ ቤቶችን ልገነባ ነው አለ
አስተዳደሩ ከቤት አልሚዎች ጋር ስምምነት ፈርሟል
የቤት ችግርን ለመፍታት በተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሀ-ግብር ማሳካት የተቻለው 30 በመቶው ብቻ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግስትና በግል አጋርነት 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ከቤት አልማዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
አስተዳደሩ የከተማዋን "የቤት ችግር" ለመፍታት አልሞ ስምምነቱን መፈጸሙን ገልጿል።
መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋን ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የቤት ፍላጎት ለማሟላት መንግስት ጥረት ማድረጉን መቀጠሉና ለቤት ገንቢዎቹ በቂ መሬት ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ከንቲባዋ በመንግስት ጥረት ብቻ የቤት ፍላጎትን ማሟላት ባለመቻሉ የግሉ አልሚዎች በቤት ግንባታው እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውንም የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከንቲባዋ አክለውም ቤቶቹን በጥራትና በፍጥናት በመገንባት የነዋሪውን ፍላጎት ለማሟላት ቤት አልሚዎች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሀ-ግብር ቢጀምርም፤ ማሳካት የቻለው ግን 30 በመቶውን ብቻ ነው።
መርሀ ግብሩ ከመጓተቱ ባሻገር ለሙስና ተጋላጭ በመሆኑ የከተማዋን ነዋሪዎች አንገብጋቢ የቤት ችግር በፍጥነት መመለስ እንዳልቻለ ተደጋግሞ ይገለጻል።
የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ መርሃ ግብሩ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት ባለመምጣቱም ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን እያማተረ ነው።
የመንግስትና የግል አልሚዎች አጋርነት (ፒ ፒ ቲ) የዚህ ጥረት አንድ አካል ነው ተብሏል።