“ቪያግራ”በአዲስ አበባ አሳሳቢ በሆነ መልኩ ሽያጩ የደራው መድኃኒት
በሀኪም ትዕዛዝ ብቻ መሰጠት የሚገባው ቪያግራ በሞተረኞችና በጀብሎ አዟሪዎች በመሸጥ ላይ ነው
የፋርማኮሎጂ ባለሙያዎች ደግሞ ቪያግራን ከሀኪም ትዕዛዝ ውጪ መውሰድ ለውስብስብ የጤና ችግሮች ይዳርጋል ብለዋል
"ሲልደናፊል" በሚል ሳይንሳዊ ስያሜው የሚታወቀው መድሀኒት ብዙዎች ግን "ቪያግራ" በሚለው ስሙ ያውቁታል።
የመድሀኒቱ ስያሜ ወደ ቪያግራ የተቀየረው መድሀኒቱ መጀመሪያ ላይ ከተሰራበት ምክንያት ውጪ ተጨማሪ የሚሰጣቸው ጥቅሞችን እንደሚሰጥ ከተረጋገጠ ጊዜ በኋላ እንደሆነ ነው።
በፈረንጆቹ ከ1996 ጀምሮ ጥቅም ላይ እንዲውል የአሜሪካው ፌደራል መድሀኒት ባለስልጣን ለልብ እና የደም ግፊት ህመምተኞች እንዲሰጥ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደዋለ ይገለጿል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በሻይዘር የመድሀኒት አምራች ኩባንያ እንደተመረተ የሚገለጸው ይህ መድሀኒት ቀስ በቀስ ከስንፉተ ወሲብ ጋር በተያያዘ ችግር ለገጠማቸው ወንዶች በእንክብል እና በመርፌ መልኩ ለታካሚዎች መሰጠት ጀምሯል።
በኢትዮጵያም ይህ መድሀኒት በሀኪሞች ትዕዛዝ ለታካሚዎች ከሚሰጡ መድሀኒቶች መካከል አንዱ ሲሆን ከህገወጥ መድሀኒት ዝውውር ጋር በተያያዘ ብዙ ተሳታፊዎች ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይታመናል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትም ክትትል ከሚያደርጉባቸው የመድሀኒት አይነቶች መካከልም ዋነኛው ነው።
አል ዐይን አማርኛ በዚህ መድሀኒት ዙሪያ ገበያ ላይ እንዴት እየተሸጠ እንደሆነ፣ ስለ ተጠቃሚዎቹ ማንነት፣ የዝውውሩ ተሳታፊዎች እና ከዚህ መድሀኒት ጋር በተያያዘ ህክምናው እንዴት ይሰጣል እና ሌሎችንም ጉዳዮች ለመዳሰስ ሞክሯል።
በሀኪም ትዕዛዝ ብቻ መሰጠት እንዳለበት የሚገለጸው ይህ መድሀኒት በህጋዊ መንገድ በህክምና ተቋማት የሚሰጥ ቢሆንም ብዙዎች ግን እንደ ማንኛውም ሌሎች ሸቀጦች እየገዙ እንደሚጠቀሙት አረጋግጠናል።
አል ዐይን በመድሀኒት መሸጫ ወይም ፋርማሲ ቤቶች፣ ምሽት ቤቶች፣ ለዚህ ሽያጭ በሚል በተፈጠሩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መድሀኒቱ እየተሸጠ እንደሚገኝም ማወቅ ችሏል።
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ መድሀኒት ቤቶች መድሀኒቱን ገዢ መስለን ባደረግነው ምልከታ የሀኪም ትዕዛዝ እንድናመጣ የጠየቁን የመድሀኒት ባለሙያዎች ቢኖሩም ብዙዎቹ ግን ያለ ሀክም ትዕዛዝ መድሀኒቱን ሸጠውልናል።
ሌላኛው ይህ መድሀኒት በህገወጥ መንገድ በስፋት የሚሸጥበት መንገድ ሆኖ ያገኘነው የማህበራዊ ትስስር ገጾች ናቸው።
ለዚሁ አገልግሎት ተብሎ የተከፈቱ እና በመቶ ሺዎች ተከታይ ያሏቸው ትስስር ገጾች ላይ መድሀኒቱን ፈላጊ መስለን ባደረግነው ሂደት ያለንበት ድረስ ይህ መድሀኒት መጥቶልናል።
እነዚህ መድሀኒት ሻጮች ሁለት አይነት መድሀኒት ማለትም የሚዋጥ እና የሚቀባ መድሀኒት እንዳላቸው መድሀኒቱንም ከ2ሺህ 500 እስከ 4ሺህ 500 ብር ድረስ እንደሚሸጡ አረጋግጠናል።
እነዚህ መድሀኒትን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በመሸጥ ላይ ያሉ ወገኖች መድሀኒቱ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሌሏቸው ለደንበኞቻቸው በግልጽ ይናገራሉ።
ሌላኛው ይህ መድሀኒት የሚሸጥበት መንገድ የምሽት መዝናኛ ቤቶች አካባቢ ሲሆን በተለይም በነዚህ አካባቢዎች ሌላ ስራ በሚሰሩ ማለትም ጥበቃ፣ ጀብሎ አዟሪዎች እና ሌሎች ስራዎችን በሚሰሩ ሰዎች አማካኝነት በመሸጥ ላይ ይገኛል።
እነዚህ አካላት ይህን መድሀኒት ለደንበኞቻቸው አንዷን እንክብል መድሀኒት ከ50 ብር እስከ 500 ብር እንደሚሸጡም ሰምተናል።
እንደ ሌሎች ሸቀጦች በየትኛውም ቦታ እየተሸጠ ያለው ይህ መድሀኒት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ መወሰዱ የራሱ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሚኖሩት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፋርማኮሎጂ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር መብራቱ እያሱ እንዳሉት ቪያግራ መድሀኒት የስንፈተ ወሲብ ችግር ላለባቸው ሰዎች ብቻ በሀኪሞች የሚሰጥ ነው ብለዋል።
"ቪያግራ ሰዎች በራሳቸው እየገዙ የሚወስዱት መድሀኒት አይነት አይደለም" የሚሉት መምህር መብራቱ ያለ ህክምና ትዕዛዝ በሚወስዱ ሰዎች ላይ ብዙ ጉዳቶችን ያስከትላል ሲሉም አክለዋል።
ሀኪሞች ይህን መድሀኒት ለታካሚዎቻቸው ሲያዙ የታካሚው እድሜ፣ የደም ግፊት አለመኖሩን፣ የልብ ምት ሁኔታን እና ሌሎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ካወቁ በኋላ ብቻ እንደሚያዙም መምህር መብራቱ ተናግረዋል።
ይህ መድሀኒት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ከተወሰደ ለፊንጢጣ መድማት፣ ለደም ግፊት፣ ለጡንቻ ህመም፣ ተቅማጥ፣ መድማት፣ ለቆዳ መቅላት፣ ለአይን ህመም፣ ላልተለመደ ውፍረት፣ ለእንቅልፍ መዛባት እና ከልብ ጋር ለተያያዙ ህመሞች ሊዳርግ ይችላልም ተብሏል።
ያለ ሀኪም ትዕዛዝ የወሲብ ማነቃቂያ መድሀኒት መውሰድ በቪያግራ ላይ ዘላቂ እና ጥገኛ የሆነ የወሲብ ህይወት እንዲኖረን ሊያደርግ ይችላልም ብለዋል።
ስንፈተ ወሲብ መኖር አለመኖሩ የሚረጋገጠው በሐኪም በሚደረግ ምርመራ እና ክትትል ብቻ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መብራቱ፤ ሁሉም የስንፈተ ወሲብ ችግር በመድሀኒት እንደማይፈታም ተናግረዋል።
በመሆኑም ሰዎች ስንፈተ ወሲብ አጋጥሞኛል ብለው ሲያስቡ መድሀኒት በራሳቸው ገዝተው ከመጠቀም ይልቅ ወደ ህክምና ተቋማት በመምጣት ክትትል ማድረጉ ትክክለኛው እና ብቸኛው መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዚህ ችግር ሰላባ የሆኑ ወንዶችም ሆኑ ችግሩ ሳይኖርባቸው መድሀኒቱን በተደጋጋሚ እየወሰዱ ያሉ ሰዎች ከዚህ ችግር ቀስ በቀስ እንዲላቀቁ ወደ ህክምና ተቋማት እንዲመጡም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መድሀኒት እና ምግብ ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድሀኒቶች በገበያው ውስጥ እንዲኖር ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ጠቅሶ ቪያግራን ጨምሮ ሌሎች መድሀኒቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከምትዋሰንባቸው ሁሉም ሀገራት በኩል ህገወጥ መድሀኒቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ጥብቅ ፍተሻ ይደረጋል የሚለው ባለስልጣኑ ይሁንና ሀገሪቱ የምትዋሰንባቸው ቦታዎች ከመስፋቱ እና በሌሎች ምክንያቶች ህገወጥ መድሀኒቶች በገበያው ውስጥ እንዳሉ በየጊዜው በሚደረጉ ክትትል ማረጋገጡንም ጠቁሟል።
በባለስልጣኑ የመድሀኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ረዳት ዳይሬክተር መንግስቱ እንዳለው ለዓልዓይን እንዳሉት
የህገወጥ መድሀኒት ሽያጭ በገበያው ላይ ያለው ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ጥናት ማሰራቱን ተናግረዋል ።
ይህ ጥናት በቅርብ ቀናት ውስጥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በተገኙበት ይፋ ይደረጋል ያሉት አቶ መንግሥቱ በዚህ ጥናት መሰረት ከዚህ በፊት ከሚደረገው የቁጥጥር ስራ በተጨማሪ አዳዲስ የመድሀኒት የክትትል እና ቁጥጥር አሰራሮች ሊዘረጉ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ሙያዊ ስነ ምግባሩን ተከትለው መድሀኒት የሚሸጡ ባለሙያዎች ቢኖሩም በዛው ልክ ሀላፊነት የማይሰማቸው የመድሀኒት ሽያጭ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል ።
ሙያቸውን አክብረው በማይሰሩ ሙያተኞች አማካኝነት ቪያግራን ጨምሮ ሌሎች ያለ ሀኪም ማዘዣ የማይሸጡ መድሀኒቶችን የሚሸጡ አሉ የሚሉት አቶ መንግሥቱ ሰዎች ለውስብስብ ችግሮች ከመጎዳታቸው ባለፈ ይህ በሽታ አምጪ ቫይረሶች እና ባክቴሪያዎች መድሀኒቶችን እንዲላመዱ እያደረገም ነውም ብለዋል።
እስካሁን በተደረገ ቁጥጥር 58 ህገወጥ መድሀኒት አዘዋዋሪዎች ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም አክለዋል።
ከተያዙት 58 አዘዋዋሪዎች ውስጥ 12ቱ ላይ በተደረገ የህግ ሂደት ጥፋተኛ ተብለው በፍርድ ቤት ከአንድ ዓመት እስከ 10 ዓመት ቅጣት ሲተላለፍባቸው ቀሪዎቹ ደግሞ የህግ ሂደታቸው መቀጠሉን ነግረውናል።
እኛም ጥብቅ ቁጥጥር እያደረግን ቢሆንም ህብረተሰቡ ካላገዘ ውጤታማ ልንሆን ስለማንችል ህዝቡ ህገወጥ የመድሀኒት ዝውውርን ሲመለከት በነጻ የስልክ መስመር 8482 ላይ በመደወል ሊያግዘን ይገባል ሲሉም አቶ መንግሥቱ ጥሪ አቅርበዋል።
የህግ አስከባሪ አካላት ከዚህ በፊት መድሀኒትን በህገወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የተያዘን ተጠርጣሪ ሞባይል ከሰረቀ ሰው ጋር እኩል የማየት ልምድ ነበር የሚሉት አቶ መንግሥቱ አሁን ላይ ጉዳቱን የመለየት እና ትኩረት ከመስጠት አንጻር መሻሻል ታይቷልም ብለዋል።