ኢኮኖሚ
በአድማ በተሳተፉ ባለታክሲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ
ታክሲዎች ከታሪፍ እና ከቅጣት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው አድማ የጀመሩት
ዛሬ በአዲስ አበባ ተሳፋሪዎች ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት ገጥሟቸዋል
በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት ተሳፋሪዋች በታክሲ እጦት ሲንገላቱ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከወትሮው የተለዩ ረጃጅም ሰልፎችም ተስተውለዋል፡፡
‘ታሪፍ አነሰን’ እንዲሁም ‘በትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች የተጋነነ ቅጣት እየተቀጣን ነው’ በሚሉ ምክንያቶች አድማ የመቱ ታክሲዎች መኖራቸው ተሰምቷል።
አል ዐይን አማርኛ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን ስለጉዳዩ ጠይቋል።
የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አከለ “የተወሰኑ ባለታክሲዎች ዛሬ ወደ ስራ እንዳልገቡ እናውቃለን” ብለዋል፡፡ “የታክሲ ባለቤቶች ታሪፍ እንዲሻሻልላቸው ጠይቀውናል ፤ በዚህም የህዝብን የመክፈል አቅም እና የነዳጅ ዋጋን ታሳቢ ያደረገ ማሻሻያ ተደርጓል” ሲሉም ገልጸዋል።
ይሁንና ከላይ ከተቀመጡት ምክንያቶች ውጭ “ዝም ብለን የታሪፍ ማሻሻያ አናደርግም” ያሉት ኃላፊው “በዛሬው አድማ ላይ በተሳተፉት ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።
በአድማው የተሳተፉት “ጥቂት ታክሲዋች ናቸው” ያሉት ኃላፊው በከተማው የትራንስፖርት ችግር እንዳይፈጠር ፐብሊክ ባስ፣ ሸገር ባስ እና ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን በስፋት በመጠቀም ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።