ያረጁ የአዲስ አበባ ላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች ሊተኩ ነው
በአዲስ አበባ የሚገኙ ያረጁ የላዳ ታክሲዎች በአዳዲስ ታክሲዎች ሊተኩ ነው ተባለ፡፡
ለዚሁ ሲባል የታክሲ ባለቤቶችን ከባንክ ጋር የማስትሳሰር ስራ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የታክሲና የሀይገር ባስ ማህበራት ለተገልጋዩ ክብርን በመስጠት ለማገልገል የሚያስችል መርሐ ግብር ይፋ ማድረጊያ መድረክ 13 የታክሲ እና ሶስት የሀይገር ባስ ማህበራት በተገኙበት ተከናውኗል።
መርሐ ግብሩ በተለይ ለአረጋውያን፣ ለነፍሰጡሮች እና ለአካል ጉዳተኞች በተሻለ መንገድ ለማገልገል የሚያግዝ ነው ተብሏል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ኢ/ር ታከለ ኡማ አነስተኛ ታክሲዎችና ሀይገር ባሶች ለነዋሪው እየሰጡ ላሉት አገልግሎት አመስግነዋል።
የታክሲ ባለንብረቶች በተለያዩ ጊዜያት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አስተዳደሩ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ያረጁ የከተማዋን አነስተኛ ታክሲዎች በአዳዲስና ከፍ ያለ የመጫን አቅም ባላቸው ታክሲዎች እንዲተኩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመድረኩ አንስተዋል።
የታክሲና የሀይገር ባስ ባለንብረቶች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ሚያከናውናቸው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።