በ6 ወራት ውስጥ 130 የሀገር ባለውለታ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ዊኪፒዲያ ላይ ማስፈር ችያለሁ- እዝራ እጅጉ (ጋዜጠኛ)
የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በኢንተርኔት ላይ አለማግኘቱ ወደዚህ ስራ እንዳስገባውም ይናገራል
በቀጣይ በ1 ዓመት ውስጥ የ1 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ለማስፈር እየሰራ መሆኑንም ተናግሯል
በ6 ወራት ውስጥ 130 የሀገር ባለውለታ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ዊኪፒዲያ ላይ ማስፈር መቻሉን የተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሙዩኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ እዝራ እጅጉ አስታወቀ።
ዊኪፒዲያ ከ16 ዓመት በፊት የተቋቋመ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለ አማርኛን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚነገሩ ቋንቋዎች መረጃዎች የሚጫኑበት ድረ ገፅ ነው።
የተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሙዩኬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የሀገር ባለውለታ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በዚህ ድረ ገጽ ላይ ማስፈር ጀምሯል።
ጋዜጠኛ እዝራ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ የመገናኛ ብዙሃን፣ የኪነጥበብ፣ በመንግስታዊ የስራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎችን ግለ ታሪክ በቀላሉ ለማግኘት እንዲቻል በማሰብ ስራውን መጀመሩን ይናገራል።
“በኢትዮጵያ የተመረተ” የሚል መኪና የመስራት ህልሙን ያሳካው ኢትዮጵያዊ
እዝራ እንዴት ይህን ስራ ጀመረ? ለሚለው ጥያቄ፤ “ከድሮ ጀምሮ ዊኪፒዲያ ላይ የሚገባው ማነው እያልኩ አስብ ነበረ፤ ወደ ስራ ዓለም ከገባሁ በኋላም የውጭ ዜጎችን ታሪክ በኢንተርኔት ላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፤ የኢትዮጵያውያንን ግን ማግኘት በጣም ከባድ ነበረ” ይላል።
“ከ6 ወር በፊት ግን መጀመር አለብኝ የሚል ሀሳብ መጣልኝ፤ ለዚህም ከቅርብ ሰዎች ማለትም በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ባሉት ጓደኞች ጀመርኩ” የሚለው እዝራ፤ መስፈርት ካወጣ በኋላ ታሪካቸውን ጽፈው እንዲልኩለት በማድረግ ወደ ዊኪፒዲያ ማስገባት እንደጀመረ ይናገራል።
“ሁሉም ሰው ባለታሪክ ነው፤ ሁሉም ሰው ደግሞ ባለታሪክ አይደለም” የሚለው እዝራ በዚህ በዊኪፒዲያ ላይ ታሪካቸውን የሚሰንድላቸውን ሰዎች ጋዜጠኛ፣ አርቲስት አሊያም ፖለቲከኛ ስለሆነ ብቻ ታሪኩን አናሰፍርም፤ አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ጎበዝ ሰዎች ታሪክ ነው የሚሰነደው ይላል።
በመጀመሪያ ስራውን ብቻውን መጀመሩን የሚናገረው እዝራ፤ በኋላ ላይ ግን የዊኪፒዲያ ቦርድ ማቋቋሙንም እና የቦርዱ ስራም ታሪካቸው ለሚፃፍላቸው ሰዎች መስፈርትን ከማውጣት ጀምሮ እነማን ቀድመው ይፃፉ፤ እነማንስ ይቆዩ የሚለውን ይወስናል ሲልም ተናግሯል።
“የሰዎችን ታሪክ ዊኪፒዲያ ላይ ለማቅረብም 11 መስፈርቶች አሉ” የሚለው እዝራ፣ ከእነዚህም ውስጥ በተሰማራበት ሙያ ላይ ያለው ጽናት፣ ስራውን በጥራት የሚሰራ፣ የሀገር ፍቅር ያለው፣ ተቀጣሪ ሆኖ የሚሰራ ከሆነም ከተቀጠረበት ስራ ውጪ ሌላ አስተዋጽኦ ያበረከተ እና በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ የሚሳተፍ፤ ይህም በቅርብ ሰዎቹ ሊሰመከር የሚችል ሊሆን ይገባል የሚሉት ተጠቃሽ መሆናቸውን ይናገራል።
በዚህም መሰረት ሰዎችን በመምረጥ ታሪካቸውን መስራት መጀመሩን የሚናገረው እዝራ፤ በመስፈርቶቹ መሰረት የራሳቸውን ታሪክ ፅፈው እንዲያቅርቡ በማድረግ እንዲሁም በቃለ መጠይቅ፣ በጥናት እና በምስክርነት ታሪኮችን እንደሚሰበስብ አስታውቋል።
በዚህ መልኩም ስራውን ከጀመረ አንስቶ ባለፉት 6 ወራት የ130 ኢትዮጵያውያንን ታሪክ ሰንዶ በአማርኛ ዊኪፒዲያ ላይ መጫን መቻሉንም ተናግሯል።
በድረ ገጹ ላይ ታሪካቸው የተሰራላቸው ሰዎች ከልጅነት ጀምሮ የተነሱት ከ2 ሺህ በላይ ፎቶግራፎች በዊኪፒዲያ ላይ መጫኑንም አስታውቋል።
ታሪካቸው ከተሰራላቸው ውስጥም የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ፣ የዶቼ ቬሌ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ፣ የጦቢያ ጋዜጣ መስራች ሙሉጌታ ሉሌን ጨምሮ የቀድሞ እና የአሁን ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት ተናግሯል።
መጀመሪያ ከመነሻው የ1000 ሰዎችን ታክ ለመስራት እቅድ ይዞ መነሳቱን የሚናገረው እዝራ፤ ሆኖም ግን በርካቶች ምን ሰርቻለው በሚል ስለሚፈሩ የ130 ሰዎችን በመስራት የእቅዱን 12 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል።
በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ በተለያዩ መስኮች ማለትም በመምህርነት፣ በፖለቲካ ኃላፊነት፣ በህክምና፣ በጋዜጠኝነት፣ በስፖርት፣ በኪነጥበብ እና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የ1 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በዊኪፒዲያ ላይ ለማስገባት እቅድ መያዙንም ተናግሯል።
ይህንን ስራ በመጀመሩም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከበርካታ ተቋማት እና ግለሰቦች ማበረታቻዎችን እያገኘ መሆኑንም አስታውቋል።