ፖለቲካ
በምዕራብ አርሲ ዞን የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ ማንነታቸው ባለታወቀ ሰዎች ተገደሉ
ግለሰቡ መጋቢት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ነው የተገደሉት ተብሏል
የወረዳውን አስተዳዳሪ መገደል የሄበን አርሲ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ቡሊዬ ማንነታቸው ባለታወቀ ሰዎች ተገደሉ።
አቶ በሪሶ ቡሊዬ በትናትናው እለት ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ገደማ ላይ ወደቤታቸው በመግባት ላይ እያሉ መገደላቸው ተሰምቷል።
አስተዳዳሪው ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቀ ሰውች በተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ማለፉንም የሄበን አርሲ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅትም በአቶ በሪሶ ቡሊዬን የገደሉ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል እተሰራ መሆኑንም የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አክሎ ገልጿል።
በሚኒስትር ማዕረግ የመለስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲም በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ የሄበን አርሲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በሪሶ ቡሊዬ ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አወሉ የተሰማቸውን ሀዘንም ግልጸዋል።