ትናንት በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በፈፀመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ህይወታቸውን አጥፍቷል
በምእራብ ወለጋ ዞን ኦነግ ሸኔ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን ክልሉ አስታወቀ
በትናትንው ዕለት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቀናቲ ቀበሌ ኦነግ ሸኔ ጨለማን ተገን በማድረግ የሽብር ጥቃት መፈጸሙን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
በፈጸመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉንም የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ መግለጫው ያለው ነገር የለም፡፡
ሰላማዊ ዜጎችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ህይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጿል፡፡ የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ “የጥፋት ሀይሎቹ” መንግስት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሰራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም በጭቃኔ የተሞላ ተግባር በህዝቡ ላይ እየፈፀሙ መሆናቸውን ነው ያስታወቀው፡፡ ኦነግ ሸኔ እና ህወሃት ፣ ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጿል፡፡
በተለያዩ ወቅቶችም የግጭት አጀንዳዎችን በማዘጋጀትና በሚዲያ በማሰራጨት እንዲሁም በህገ ወጥ መንገድ በገቡ የጦር መሳሪያዎች በፀጥታ ሀይሎች፣ በመንግስት መዋቅር እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የግድያ እርምጃ በመስወድ ችግሮችን ሲፈጥሩ መቆየታውን አሰታውቋል፡፡
ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በተፈፀሙ በእነዚህ ተግባራትም በህብረተሰቡ ላይ የስነ ልቦና ጫና እንዲፈጠር፣ በስጋት እንዲሞላ እና ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ራሱን ቆጥቡ በረሃብ እና በጥማት እንዲጎዳ እያደረጉ ስለመሆኑም ነው ክልሉ የገለጸው፡፡
በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አቅጣጫ በሚገኙ ዞኖች ህፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ወጣቶች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እንዲገደሉ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ፣ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው እንዲሁም የስነ ልቦና ጉዳት እንዲደርስባቸው እና እንዲፈናቀሉ መደረጉን የኦሮሚ ክልል አስታውቋል፡፡