በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳደሪ ተገደሉ
በአማራ ክልል ባለፈው ሚያዝያ ወር የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል
በአማራ ክልል የአሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳደሪ አቶ አህመድ አሊ በትናንትናው እለት በከሚሴ ከተማ መገደላቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳደሪ ተገደሉ።
በአማራ ክልል የአሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አስተዳደሪ አቶ አህመድ አሊ በትናንትናው እለት በከሚሴ ከተማ መገደላቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አቶ አህመድ የጁምካ ሶላት አድርሰው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ "በጽንፈኞች በተተኮሰባቸው ጥይት" ተመተው ህይወታቸው አልፏል።
ግድያ ፈጽመዋል ያላቸውን "ጽንፈኞች" በስም ያልጠቀሰው የክልሉ መንግስት መግለጫ አቶ አህመድ "ጽንፈኝነትን አምርረው የሚታገሉ፣ በተሰማሩበት ሁሉ የህዝብን ጥቅም የሚያስከብሩ" ነበሩ ብሏል።
መግለጫው "ፅንፈኝነት መሪዎችን በመግደል የሚያሸንፍ ቢመስልም የበለጠ ትግላችንን መራርና ፈጣን በማድረግ እንደ ብረት የሚያጠነክረን እንጅ ወደ ኋላ የሚመልሰን አይደለም" ሲል አክሏል።
የክልሉ መንግስት በዚህ መግለጫው ጽንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች በስም ባይጠቅስም፣ ከዚህ በፊት ባወጣቸው መግለጫዎች በዞኑ መንግስት "ሸኔ" በሚል በአሸባሪነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጦር እንደሚንቀሳቀስ ሲገልጽ ቆይቷል።
ለብሔረሰብ ዞኑ አጎራባች በሆነው ሰሜን ሸዋ ዞን በተለያየ ጊዜ ለደረሰው ግድያ እና የንብረት ውድመት እነዚህ ታጣቂዎች ተጠያቂ ተደርገዋል።
በአማራ ክልል ባለፈው ሚያዝያ ወር የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የመንግስት ባለስጣናት ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ የሺጥላ ግድያ በጉልህ የሚታወሰ ነው።
የፌዴራል መንግስት ባለፈው ሐምሌ ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ በኋላ ቀጥሎ እየተካሄደ ባለው የፈደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ግጭት በንጹሃን ሰዎች ላይ ከሚደረሰው መጠነሰፊ የመብት ጥሰቶች በተጨማሪ በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ ኃላፊዎች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።
በክልሉ እስካሁን በቀጠለው አብዛኛውን የመብት ጥሰት የሚፈጽሙት የመንግስት የፈጥታ ኃይሎች መሆናቸውን የተብት ተቋማት ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።