ከፍተኛ የጦር አዛዥ የተገደለበት ሄዝቦላ 200 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል አስወነጨፈ
የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት በጥቃቱ በሰዎች ላይ የደረሰ ጥቃት የለም ብሏል
የሊባኖሱ ሄዝቦላ ታጣቂ የጦር አዛዡን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ መጠነሰፊ የድሮን እና የሮኬት ጥቃት አድርሷል
ከፍተኛ የጦር አዛዥ የተገደለበት ሄዝቦላ 200 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላ ታጣቂ የጦር አዛዡን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ መጠነሰፊ የድሮን እና የሮኬት ጥቃት አድርሷል።
በጋዞ ጦርነት ምክንያት የተቀሰቀሰው በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላ እና በእስራኤል መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን ሁሉቱም ወገኞች እንደማይፈልጉት ወደሚገልጹት አጠቃላይ ጦርነት ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
የቅርብ ጊዜ ግጭቶች እንደባለፉት ዘጠኝ ወራት ሁሉ በድንበር አካባቢ እየተካሄዱ ነው፤ ቤሩት እና ሌሎች የሊባኖስ ክፍሎች ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቦምብ ፍንዳታ እየተናጡ ናቸው።
የሊባኖስ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል ጄቶች በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጥቃት እያደረሱ ነው። ሄዝቦላ ባለፈው ረቡዕ በእስራኤል ጥቃት በደቡብ ሊባኖስ የተገደለውን ወታደራዊ አዛዥ ሞሀመድ ናስር ግድያን ለመበቀል በ200 ሮኬቶች እና በርካታ ድሮኖች በ10 የእስራኤል ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልጿል።
ናስር በግጭቱ በእስራኤል የአየር ጥቃት ከተገደሉት ከፍተኛ አዛዦች አንዱ ነው።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው "200 ሮኬቶች እና 20 አጠራጣሪ ኢላማዎች ከሊባኖስ በኩል የእስራኤልን ድንበር ሲያቋረጡ ተለይተው" አብዛኞቹ በእስራኤል የአየር ኃይል ተመትተዋል።
የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት በጥቃቱ በሰዎች ላይ የደረሰ ጥቃት የለም ብሏል። የእስራኤል ጦር የተወሰኑ ድሮኖች እና ፍንጥርጣሪዎች እሳት ማስነሳታቸውን ገልጿል።
የእስራኤል አየር ኃይል በራምየህ እና ሀውላ የሚገኙ የሄዝቦላ ወታደራዊ መዋቅሮችን መትቷል።
የሄዝቦላ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆነው ሀሽም ሰይፈዲን፣ ናስርን ለማስታወስ በተዘጋጀ ፕርግራም ላይ ቡድኑ ማጥቃቱን እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ሄዝቦላ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ወደ ተኩስ ልውውጥ የገባው፣ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን አጋርነት ለማሳየት ነው።