3.4 ትሪሊየን ዶላር ግብይት ይፈጥራል የተባለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ምን ላይ ይገኛል?
የቀረጥ ታሪፍ እና ሸቀጦች የተመረቱበትን ሀገር ለይቶ ለግብይት የሚፈቅድ ሥርዓትን ማበጀት ላይ በፈራሚ ሀገራቱ መካከል ያለው ውዝግብ አልተፈታም
የሰፊ ገበያ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ከሸማችነት ባለፈ ምርቶቿን ለአህጉሩ ገበያ በማቅረብ እንዴት ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው
የአፍሪካ ህብረት በመጋቢት 2010 ላይ በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ ባደረገው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነበር የአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ስምምነት የተፈረመው።
ይህ ስምምነት ከዓለም ንግድ ድርጅት ቀጥሎ በርካታ ሀገራት የፈረሙት ሁለተኛው ግዙፍ የንግድ ስምምነትም ነው።
አሁን ላይ ከኤርትራ በቀር 54 ሀገራት የፈረሙት ስምምነቱ በዋናነት በገቢ ዕቃዎች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ 97 በመቶ እና ከዛ በላይ የማስቀረት ግብ አለው።
ጥር 2013 ዓ.ም ወደ ስራ የገባውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ከ1.3 ቢሊየን በላይ የሚሆኑ የአፍሪካን ህዝቦች በማቀራረብ፤ 3.4 ትሪሊየን ዶላር ግምት የሚሆን አህጉራዊ ገበያን እንደሚፈጥር ተስፋ ተደርጎበታል።
በስምምነቱ መሰረት ከ5,800 በላይ የሌሎች ሀገራት ምርቶች ያለ ታሪፍ ወደ ገበያዋ ገብተው እንዲሸጡ የተስማማችው ኢትዮጵያ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን ጨምሮ የ453 ምርቶችን የታሪፍ ከለላ ለተወሰነ ጊዜ አላነሳም ማለቷ ይታሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት በቅርብ ጊዜ ያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደካማ የሚባል የእርስ በእርስ የንግድ ግንኙነት ያላቸው የአህጉሪቷ ሀገራት 15 በመቶ ብቻ ምርታቸውን ሲገበያዩ 85 በመቶ ምርታቸውን ወደ አውሮፓ ፣ እስያ ሰሜን አሜሪካ እና ላቲን አሜሪካ ሀገራት ይልካሉ።
ይህ የነጻ ንግድ ስምምነትም አፍሪካውያን እርስ በእርስ ያለቸውን የንግድ ፣ ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ግንኙነት በማጠናከር ሰፊ ትሩፋት ሊኖረው እንደሚችል ታምኖበታል።
አለፍ ሲልም የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ ከውጭ የሚያስገቡት የአፍሪካ ሀገራት ትስስር ቢፈጥሩ የትራንስፖርት እና የምርት ዋጋን በመቀነስ ሸቀጦች በርካሽ ዋጋ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት አተገባበር ምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል?
አል ዐይን አማረኛ 3.4 ትሪሊየን ዶላር ግብይት ይፈጥራል የተባለው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት አተገባበር ምን አይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል? ሲል ጥያቄ አንስቷል።
በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት ዘላቂ ልማት በአፍሪካ ኢንስቲትዩት (ISDAF) ዋና ስራ አስኪያጅ እዮብ እሳቱ፤ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ በፈራሚ ሀገራት ገቢራዊ ሲሆን ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው እምነት ቢኖራቸውም አሁንም ምላሽ ያለገኙ በርካታ ጥያቄዎች መኖራቸው የታሰበለትን ግብ እንዳይመታ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት “አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ዛሬም የሚከተሉት ኋላ ቀሩ ግብርና ነው። አነስተኛ የእርሻ ባለቤቶች ከግዙፍ እና ውስብስብ የግብርና ሥራዎች ጋር መወዳደር የመቻላቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።
አፍሪካውያን ሸማቾች ርካሽ ምርቶች መፈለጋቸው አነስተኛ አምራቾች ከውጪ ሀገራት በሚገቡ ሸቀጦች ጫና ሊደርስባቸው እንደሚችል ስጋት አለ” ብለዋል።
በአፍሪካ ሀገሮች መካከል የሚታየው የምጣኔ ሐብት እና የመሰረተ ልማት ልዩነት ሌላው ለአተገባበሩ ወጥነት እንቅፋት እየሆኑ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።
ከአፍሪካ አጠቃላይ የምርት መጠን 50 በመቶውን የተቆጣጠሩት እንደ ግብፅ፣ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ በጣት የሚቆጠሩ ሀገራት ናቸው።
እንደ አቶ እዮብ ገለጻ ታድያ ምንም እንኳን ሀገራቱ በመካከላቸው የመሰረተ ልማት እና የአሰራር ትልቅ ልዩነት ቢኖርም በሰፊው ሊያመርቷቸው የሚችሏቸውን ምርቶች ለይተው እነርሱ ላይ በትኩረት የሚሰሩ ከሆነ ተወዳዳሪነታቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው ከታሪፍ ቅነሳው ጋር በተያያዘ ስምምነቱን ተግባራዊ ያደረጉ ኬንያን የመሳሰሉ ሀገራት ከአሁኑ በገቢያችን ላይ ቅናሽ አመጣብን በሚል ቅሬታ ማቅረብ መጀመራቸውን ያነሳሉ።
ሀገራት ከታሪፍ ቅነሳ የሚያጡትን ገቢ በምን አይነት መልኩ ማካካስ ይችላሉ?
ለመሆኑ ሀገራት ከታሪፍ ቅነሳ የሚያጡትን ገቢ በምን አይነት መልኩ ማካካስ ይችላሉ? ሲል አል አይን ዶክተር ቆስጠንጢኖስን ጠይቋል።
“ሁሉም ሀገር አንድ አይነት ምርት አያመርትም ለምሳሌ ኢትዮጵያን ብትወስድ ግብርና ትልቁ መወዳደርያ አቅሟ ነው። ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ፍራፍሬ፣ ቡና እና ሌሎችም የግብርና ምርቶች ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ እየተደረገላቸው በሰፊው የሚመረቱ ከሆነ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በሌሎች ሀገራት የሚወሰድብንን ብልጫ ማመጣጠን ይቻላል”።
ከዚህ ባለፈ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም ማሳደግ ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ከታሪፍ ነጻ በሚገቡ ርካሽ ምርቶች የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዳይጎዱ እሴት ጨምረው ለገበያ የሚወጡ ዘርፎች መጠናከር እንደሚኖርባቸው ተገልጿል።
እንደ ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት በምርታማነት እና በአለም አቀፍ ንግድ ሰፊ አቅም ማዳበራቸውን የሚያነሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ኢትዮጵያ ምርት ማራገፍያ እና ሸማች ብቻ እንዳትሆን ጥንቃቄ መደረግ እንደሚኖርበት ያነሳሉ።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ይህን ቢሉም ከፍተኛ የሚታረስ መሬት፣ ውሀ እና የሰው ሀይል ባለቤት የሆኑት የአፍሪካ ሀገራት ለዘርፍ የሚመድቡት በጀት በአብዛኛው ከ2-5 በመቶ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአንፃሩ የበለፀጉት አገራት እስከ 10 በመቶ እና ከዛ በላይ ይመድባሉ።
የዘላቂ ልማት በአፍሪካ ኢንስቲትዩት (ISDAF)ዋና ስራ አስኪያጅ እዮብ እሳቱ እዮብ እሳቱ እንደሚሉ አሰራርን ማዘመን እና ለስምምነቱ መሳለጥ የሚያግዙ ሂደቶችን ማደላደል ለተወዳዳሪነት ትልቅ አቅም ከሚፈጥሩ ነጥቦች መካከል አንዱ ነው፡፡
ለአብነትም “በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ የነጻ የገበያ ቀጠና ውስጥ 15 ኢንቨስተሮች እየሰሩ ይገኛሉ ከዚህ ውስጥ 9ኙ ከውጭ የመጡ ባለሀብቶች ናቸው፤ በቀጣይ ደግሞ በቀጠናው ውስጥ ለመካተት ቁጥራቸው 300 የሚሆኑ አልሚዎች ተመዝግበዋል። ይህ ሀገሪቱ በግብርና እና ማንፋክቼሪንግ በአህጉሩ ገበያ ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ የሚሳድግላት ነው” ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቅስጠንጢኖስ በበኩላቸው በበቂ ሁኔታ ምርት የሌለው ሀገር በነጻ ንግድ ቀጠናው ከፍተና ተጽእኖን እንደሚያስተናግድ ይናገራሉ።
“በኢትዮጵያኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሰሩ አልሚዎችን ብንመለከት አብዘኞቹ የውጭ ባለሀብቶች ናቸው፤ ሀገሪቱ ልማት ላይ መሳተፍ የሚችል የባለሀብት ቁጥር ሳያንሳት በመንግስት በኩል ግን ተሳትፎዎችን ሊያሳድጉ የሚችሉ አሰራሮችን ማስተዋወቅ ላይ ቀሪ የቤት ስራ አለ” ባይ ናቸው።
ይህን ለማድረግ ከብድር እና ማበረታቻዎች አቅርቦት ባለፈ የንግድ እና የፋይናንስ አስተዳደሩን ጤናማ እንዲሁም በባለሙያዎች እንዲመራ መደረግ እንደሚኖርበት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ስምምነቱ በታቀደው ልክ ግቡን መምታቱን ለማረጋገጥ አፍሪካውን ሀገራት የቀረጥ ታሪፍን ከማንሳት ባለፈ በመሰረተ ልማት በኩል ያለባቸውን ክፍተት መሙላት፣ ውጤታማ የሚሆኑባቸው ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት፣ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብታቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር አቀናጅቶ መጓዝ እንደሚኖርባቸው ባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳባቸውን ለግሰዋል።
የአፍሪካ ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ስምምነት የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ ንግድ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2034፤ 60 በመቶ በማሳደግ የ3.4 ትሪሊዮን ዶላር ገበያ ለመፍጠር ውጥን ይዟል።
በዓለም ባንክ የ2019 መረጃ መሠረት ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ከሆነ 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ከከፋ ድሕነት፣ 70 ሚሊዮን የአኅጉሪቱን ዜጎች ደግሞ ከመካከለኛ ድህነት ያስወጣል ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም አጠቃላይ አመታዊ የምርት መጠናቸው 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ 1.2 ቢሊዮን ሸማቾች ሲኖሩት ፤በፈረንጆቹ 2035 አጠቃላይ የወጪ ንግድ መጠኑ በ29 ከመቶ የሚያድግ ሲሆን የአህጉሩ የወጪ ንግድ ደግሞ ወደ 81 ከመቶ ከፍ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡