“የሕዳሴ ግድብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ እንደ ማሳያ ሊወሰድ ይገባል”- ፌሊክስ ሺስኬዲ
የሺስኬዲና የልዑካቸው ጉብኝት የተሳካ ነበርም ተብሏል
ግድቡ ከልዩነት ይልቅ የትብብር ምንጭ ሊሆን እንደሚገባም የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር እና የዲ አር ኮንጎው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካ መሪዎች በሚፈልጉት “በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ማሳያ ሊሆን እንደሚገባ አስታወቀች፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ፌሊክስ ሺስኬዲ በአዲስ አበባ፣ካርቱም እና ካይሮ የነበራቸውን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ የሀገሪቱ የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ሺስኬዲ የትብብር ምንጭ መሆን ሲገባው የውዝግብ ምንጭ በሆነው በግድቡ ጉዳይ ዙሪያ ከሃገራቱ መሪዎች ጋር መምከራቸውን አስታውሷል፡፡
ሺስኬዲ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ መሪዎች በሚፈልጉት ነጻ አህጉራዊ የንግድ ቀጠና ውስጥ “ሞዴል ሆኖሊወሰድ ይገባል” ሲሉ ደጋግመው ማስታወሳቸውንም ጠቁሟል፡፡
ግድቡ “የትብብርና ትስስር ምሳሌ እንጂ የመጥፎ እድልና ችግር ምንጭ” መሆን እንደሌለበት በመግለጫው ተካቷል፡፡
አፍሪካ በበቂ ሁኔታ በመሰረተ ልማት የተሳሰረች እንዳልሆነች የተገለጸ ሲሆን፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጠቀሜታን ወሳኝነት ትረዳለች ብሏል መግለጫው፡፡
ሺስኬዲ የመጨረሻ መዳረሻቸው ያደረጉት በኢትዮጵያ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታም ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ እና ከጠ/ ሚ ዐቢይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በውይይቱ ግድቡ የትብብርና የጋራ ልማት ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል እና በሁለቱም ሀገራት ላይ ምንም ጉዳት በማያስከትል መንገድ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በትብብር መርህ ማዕቀፍ (ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) መሠረት ለሁሉም ወገኖች የሚጠቅም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ያላትን ፍላጎት ደግማ ትገልጻለችም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት መግለጹ ይታወሳል፡፡
የሺስኬዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለጊዜው የተቋረጠውን የሶስትዮሽ ድርድር ለማስቀጠል ሊሆን እንደሚችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ማክሰኞ ዕለት ገልጸዋል፡፡
የፕሬዝዳንቱን ጉብኝት የተመለከተው መግለጫ ግብፅ እና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ አስገዳጅ ስምምነቶች እንዲኖሩ ይፈልጋሉ ብሏል፡፡
ህልውናዬ በናይል ላይ የተመሰረተ ነው በሚልም ግብጽ ከፍ ያለ ስጋት እንዳላት ታስቀምጣለች፡፡
ኢትዮጵያ ደግሞ ግድቡ ለህዝቧ የኃይልና የመልማት ፍላጎት መሟላት ከምንም በላይ ወሳኝ እንደሆነ ደጋግማ ትገልጻለች፡፡
ግድቡ የትብብር አቅም ሊሆን እንደሚችል በመጠቆምም አፍሪካ ህብረት መር በሆነና ለሁሉም በሚሰራ ስምምነት ቁርጠኛ ሆና እንደምትቀጥልም መግለጿ ይታወሳል፡፡
ኮሚቴው ከጉብኝቱ መጠናቀቅ በኋላ በአዲስ አበባ ከአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ፣ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲኦዬ ጋር መክሯል፡፡
የኮሚቴው ጸሃፊ ከህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ኮሚቴ ጋር ተገናኝተው መምከራቸውንም ነው ያስታወቀው፡፡
ጉብኝቱ የተሳካ እንደነበርም ገልጿል፡፡