የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ወደ ሙሉ ተግባር ይገባል ተባለ
ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ እንድትጠቀም ታስቦ የህግ ማዕቀፍ እንደተቀረጸ ተነግሯል
ነጻ የንግድ ቀጠናው ቀረጥና ክፍያዎች ነጻ በመሆናቸው የዋጋ ንረት እንደሚቀንስ ተስፋ ተጥሎበታል
ነሀሴ 8 2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተመረቀው የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ሀገሪቱ ለገጠሟት የምጣኔ-ሀብት ፈተናዎች እንደ አንድ መፍትሄ ታይቷል።
ሀገሪቱ እያካሄደችው ያለችው የምጣኔ-ሀብት ማሻሻያና የ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ አካል ነው የተባለው ነጻ የንግድ ቀጠናው ከተገነባበት ከተማ ጀምሮ ለሀገሪቱ ንግድ መሳለጥ አበርክቶው ሁነኛ ነው ተብሏል።
የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ስራ አስኪያጅ ካሚል ኢብራሂም ቀጠናው ወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ እንዲመች ተደርጎ መሰናዳቱን ለአል ዐይን ገልጸዋል።
የነጻ ንግድ ቀጠናው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ፣ የወጪ ንግድን ለማነቃቃት፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም የድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ከተማነት ለማስፋፋት ፋይዳ አለው ብለዋል።
ተቋሙ፤ የማምረቻ፣ የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የሎጀስቲክስ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል። ዋነኛ ስራውም ከቀረጥ ነጻ ምርቶች እንዲገቡና እንዲወጡ ድጎማ ማድረግ እንዲሁም የተንዛዙ ስርዓቶችን ቀልጣፋ ማድረግ በመሆኑ ተስፋ ተጥሎበታል።
“እንደ ሀገር የጉምሩክ ህግ አለን፣ የባንክ ህግ አለን፣ የንግድ ህግ አለን። እዚህ ቦታ [ነጻ የንግድ ቀጠናው] እነዚህ ሁሉ ህጎች ቀለል ባለ ስርዓት ተግባራዊ ይሆናሉ” በማለት ስራ አስኪያጁ ቅልጥፍና መለያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙንና ስርዓቱን የሚመሩ የተለያዩ ህጎችና መመሪያዎችን በመንደፍ ላይ ተጠምደን ነበር የሚሉት ካሚል ኢብራሂም፤ የዝግጅት ምዕራፍ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ከሰሞኑንም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈጻሚ በተገኙበት ከባለሀብቶች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።
የቀሪውን ዓመት ቀጣይ ውጥን የተጠየቁት ስራ አስኪያጁ በሚቀጥለው ስድስት ወር ወደ ሙሉ ወደ ትግበራ (ኦፕሬሽን) መግባት እንደሆነ ገልጸዋል።
“የነጻ ንግድ ቀጠና ፈቃድ ወስደው የሚገቡ ድርጅቶችን የመምረጥ፣ የማምረቻ መስፈርቱን የሚያሟሉትን የመምረጥ፣ ሁለተኛ የገቡትን በነጻ የንግድ ቀጠና ህግ አገልግሎት ማቅረብ፣ ቀልጣፋ ስርዓት መፍጠር ፣ ዓላማውን በሚያሳካ መልኩ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ባለሀብቶች ኢንቨሰት እንዲያደርጉ መስራት ቀጣይ ስራችን ነው” ብለዋል።
ነጻ የንግድ ቀጠናው በመዳፉ ያሉትን የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክና ደረቅ ወደብን ከአየርና ከየብስ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀት የባንክና የጉምሩክ አገልግሎቶችንም ይሰጣል። ለዚህ የተመቻቸች ናት የተባለችው ድሬዳዋ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የሆነው ቀጠና እንዲከፈትባት ሆኗል።
የገቢና ወጪ ንግድ ቀረጥና ክፍያዎች ነጻ ሲሆኑና ስርዓቱ ሲቀላጠፍ የዋጋ ንረት እንዲቀንስ በማድረግም ቀጠናው አበርክቶ እንዳለው ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል። የምርቶችን የቆይታ ጊዜ በመቀነስና የተቀላጠፈ አገልግሎቱ የምርት ዋጋ ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍ ለተጠቃሚው (ለማህበረሰቡ) ይጠቅማል ብለዋል።
“እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ወጪ ብቻ ይላክ የሚባልበት አይደለም። የገቢና ወጪ ንግድ የሚተላለፍበት ቦታ ማለት ነው። ለሀገር ውስጥም የሚቀርብበት፤ ወደ ውጭም የሚላክበት ቦታ ነው። ገደብ የለውም። የቆይታ ጊዜ ይቀንሳል። ይህም ክፍያን ይቀንሳል። በመልቲሞዳል ከሚገባው በነጻ ንግድ ቀጠና የሚገባው የወጪ ልዩነት አለው። ስለዚህ ዋጋ ላይ ልዩነት ይኖራል” ብለዋል።
ካሚል ኢብራሂም እንደተናገሩት ወደቦች ላይ ረጅም ጊዜ የሚወስደውን ሂደት በመቀነስ ነጻ የንግድ ቀጠናው ውስጥ በተዘጋጁ መጋዝኖች እቃቸውን በማራገፍ፣ በመገጣጠም፣ ሪብራንድ በማድረግ ወደ ውስጥም ውጨም ምርትን መላክ ይቻላል።
ከዚህም ባሻገር የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ ለፈረመቻቸው እንደ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና የመሰሉ አህጉራዊና ክልላዊ ስምምነቶች መሰረት እንደሆነ ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል። ሀገሪቱ ነጻ የምርት ዝውውርን ከሚፈቅዱ ስርዓቶች ድርሻ እንዲኖራት ያደርጋልም ብለዋል። ለዚህም ህጎቹና ስምምነቶች ዓለም አቀፋዊ እይታ እንዲኖራቸው ተደርጓል ነው ያሉት።
ድሬዳዋ፥ ኢትዮጵያ ከምትጠቀማቸው ወደቦች በተለይም ከጅቡቲ ወደብ በ350 ኪ.ሜ ርቀት ላይ መገኘቷና ያላት የሎጀስቲክ አደረጃጀት ተመራጭ አድርጓታል።