በአለም አቀፍ ደረጃ ከተፈናቀሉ ሰዎች ግማሽ ያህሉ በአፍሪካ ይገኛሉ
በምስራቅ አፍሪካ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነገረ።
በምስራቅ አፍሪካ 20.1 ሚሊዮን ሰዎች በሀገር ውስጥ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጄንሲው በትላንትናው እለት በኬንያ ናይሮቢ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በሰኔ ወር 19 .2 ሚሊየን የነበረው የተፈናቃዮች ቁጥር በነሀሴ በ900ሺህ ጭማሪ አሳይቶ 20 .1 ሚሊዮን ላይ ይገኛል ብሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የተፈናቃይ ቁጥር አለባቸው ከሚባሉ የቀጠናው ሀገራት መካከል ሱዳን 10.2 ሶማሊያ 3.5 ኢትዮጵያ 3.3 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን በመያዝ ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡
ግጭት ፣ ጎርፍ ፣ እና የመግብ ዋስትና አለመረጋገጥ በሀገራቱ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡
የሌሎች ሀገራት ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዮችን በማስተናገድ ኡጋንዳ ቀዳሚዋ ስትሆን በሀገሪቱ 1.7 ሚሊዮን ስደተኞች ይገኛሉ። ኢትዮጵያ 1 ሚሊየን ኬንያ 906 ሺህ ስደተኞችን በማስተናገድ በደረጃ ይገኛሉ፡፡
ቀጠናው ከ67 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምግብ እጥረት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ እንደ አለም አቀፉ የምግብ እና እርሻ ድርጅት መረጃ ከሆነ ከዚህ ውስጥ 39 ሚሊየን የሚሆኑት የቀጠናዊ ድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት ድርጅት አባል ናቸው፡፡
አለም አቀፊ የስደተኞች ኤጄንሲ በመጪው ህዳር ወር ጀምሮ በቀጠናው ሀገራት አንዳንድ አካባቢዎች ይፈጠራል ተብሎ የሚጠበቀው ድርቅ በቀጠናው የሚገኝውን የምግብ እጥረት በማባባስ ተጨማሪ ተፈናቃዮችን ሊፈጥር እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ግንቦት ወር ላይ የወጡ መረጃዎች ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገረት 75.9 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ሲጠቀስ ይህም የአለምን ግማሽ ተፈናቃይ ቁጥር የሚሸፍን መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በሱዳን የተፈናቀለው የህዝብ ቁጥር ከ2008 ወዲህ በዚህ ልክ በከፍተኛ መጠን ሰዎች ሲፈናቀሉ የመጀመርያው ያደርገዋል፡፡
በምእራብ አፍሪካ የሽብረተኞች ጥቃት እና ተዋጊዎች ከመንግስት ጋር የሚያደርጉት ውግያ እየተባባሰ መምጣት በቀጣይ የተፈናቃዮችን ቁጥር ከሚያንሩ ምክንያቶች መካከል ተቀምጠዋል፡፡