ዛሬ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በምስል
ሙዚየሙ የዓድዋ ጀግና መሪዎች ሀውልትን ጨምሮ ጦርነቱን የሚያሳዩ ስዕሎችና ቅርጻ ቅርጾችን ይዟል
የአድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ውጤት መሆኑን በሚያሳይ መልኩ መሰራቱም ተገልጿል
በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በዛሬው እለት በይፋ ተመርቋል።
በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሙዚየም የኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነ ተጋድሏቸውን የሚዘክሩ ስራዎችን ይዟል።
የአድዋ ድል መሃንዲሶች አፄ ምኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንዲሁም የ12ቱ የጦር መሪዎች ሀውልትም በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛሉ።
የዓድዋ ድል የክተት አዋጅ የታወጀበት ነጋሪት በነሐስ ተሰርቶ ለእይታ ቀርቧል።
በ4ቱም አቅጣጫዎች የተለያዩ ስያሜ የተሰጣቸው የሙዚየሙ በሮችም በዓድዋ ድል ከአራቱም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሳተፉበት መሆኑን ያመለክታል ብሏል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር።
ሙዚየሙ ከምድር በታች ያለውን ሁለት ደረጃዎችን ጨምሮ 5 ወለሎች ያሉት ሲሆን፥ ከ1 ሺህ በላይ የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ በርካታ አዳራሾችና መዝናኛ ስፍራዎችንም አካቷል።