“ሰውነት የከበረበት” አድዋ ለምን አለማቀፋዊ ድል ነው ተባለ?
የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች እና የጭቁኖች የነጻነት ምልክት ለመሆን በቅቷል

አል ዐይን በርግጥስ “ኢትዮጵያውያን የአድዋን ከፍታ ተረድተነዋል ወይ? የታሪክ ድርሳናትስ ስለ አለምእቀፋዊው ድል ምን ይላሉ” ሲል የታሪክ ምሁራንን ጠይቋል
አውሮፓውያን በ1885 ለሶስት ወራት አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ በበርሊን ሲያደርጉ ከ80 አመት በፊት የገጠማቸውን ሽንፈት ዘንግተውታል።
ከ1791 እስከ 1804 ብርቱ ተጋድሎ አድርገው “ነጮችን” (ፈረንሳዮችን) ያሸነፉት የሃይቲ አብዮተኞችን እግር የሚከተሉ አፍሪካውያን ይኖራሉ የሚል ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበራቸውም።
በታሪክ ሁለተኛውና ለዘመናት የማይዘነጉት ሽንፈት ግን በኢትዮጵያ ምድር አድዋ ላይ ከ127 አመት በፊት ገጠማቸው።
“በዚህ ድልም አፍሪካን ሁለተኛ ዜጋ አድርገው ቆጥረውና ንቀው ሊበዘብዙት የያዙት የዘመናት እቅድ ጥያቄ ውስጥ ገባ” የሚሉት ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፥ ጨለማ ተደርጋ የተሳለችው አፍሪካ በአድዋ ብርሃን እንደወጣላት ያወሳሉ።
በአድዋ ጣሊያን ብቻ ሳትሆን በሃይቲዎች የተረቱት ፈረንሳውያንን ጨምሮ በበርሊኑ ጉባኤ አብረዋት አፍሪካን ለመቀራመት የዶለቱት ሁሉ መሪር ሽንፈት መጎንጨታቸውንም ነው የሚያስታውሱት።
በጂማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ከተቦ ዲቦም ለአል ዐይን አማርኛ፥ አድዋ ለመላው አውሮፓውያን አስደንጋጭ እንደነበረው ሁሉ ለአፍሪካውያን እና ለመላው ጭቁን ህዝቦች ትልቅ ብስራት እንደነበር ይገልጻሉ።
“በአድዋ ኢትዮጵያ ድል አድርጋ የሰው ልጆችን እኩልነት አውጃለች፤ በባርነት ቀንበር ውስጥ ለነበሩ ህዝቦችም የነጻነት ቀንዲል ሆናቸዋለች”ም ይላሉ።
በአድዋ ድል ማግስት ምን ተከሰተ?
የአውሮፓውያን በአፍሪካ ምድር በጥቁሮች መሸነፍ ዜና በመላው አለም ሲዳረስ ጊዜ አልወሰደበትም።
የጣሊያኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ክሪስፒ ከስልጣን ያስለቀቀው የአድዋ ድል፥ ወራሪዎችን ሲያሳፍር የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ ሆኖ የነጻነት ትግሎችን ማቀጣጠል ጀምሯል።
የአድዋ ድል ሁለተኛ አመት ሲዘከርም በለንደን የፓን አፍሪካ ኮንፈረንስ መካሄዱን ፕሮፌሰር አየለ ለዚህ አስረጂ አድርገው ያቀርቡታል።
በዚህ ጉባኤ ላይ አጼ ምኒሊክ በክብር እንዲገኙ ቢጋበዙም የደስታ መልዕክት ይዞላቸው የመጣውን ሃይቲያዊ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ቤኒቶ ሲልቬይን ወክለውት ሁለቱንም የነጻነት ፊታውራሪ ሀገራት ወክሎ መሳተፉንም ታሪክ እንደሚያወሳ ፕሮፌሰር አየለ ለአል አይን ተናግረዋል።
ከለንደኑ የፓን አፍሪካኒዝም ጉባኤ ጅማሮ አንስቶ አድዋ ከመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ንቅናቄ ጋር ተሳስሮ መቀጠሉንም ያብራራሉ።
የጂማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ከተቦም፥ አድዋ አለምአቀፋዊ ድል ሆኖ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴዎች ሁሉ መነሻ እስከመሆን መብቃቱን ይናገራሉ።
ጃማይካዊውን ማርከስ ጋርቬይ ጨምሮ የነጻነት ታጋዮች አድዋን “የይቻላል መንፈስ ማጋቢያ” አድርገው በስፋት ተጠቅመውበት ትግላቸውን አቀጣጥለውበታልም ነው የሚሉት።
በአሜሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት የሚገኙ ጥቁሮች የኢትዮጵያ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያንን ከፍተው ለእኩልነት እንዲታገሉም አድዋ መነሻው ነበር ይላሉ ዶክተር ከተቦ።
በብራዚልም በፈረንጆቹ 1915 “ኦ ሚኒሊክ” የሚል ጋዜጣ እየታተመ ይወጣ እንደነበር ያወሳሉ።
የአፍሪካ አንድነትና አድዋ
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ከጀመሩ በኋላ በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው አምነው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በ1963 ሲያቋቋሙ የአድዋ ድል መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል።
የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢ ሲ ኤ) በ1958 በአዲስ አበባ ሲከፈትም የታላቁ ድል ድርሻ መዘንጋት የለበትም የሚሉት የታሪክ ምሁራኑ፥ አድዋ የአፍሪካውያንን የነጻነት ተጋድሎ ብቻ ሳይሆን በጋራ የመቆማቸው መሰረት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
የኬንያው ጄሞ ኬንያታም ሆኑ ጋናዊው ክዋሜ ንኩርማህ፤ የጸረ አፓርታይድ ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያን የነጻነት ምልክት አድርገው ሲያቀርቡ አድዋ የማይዘሉት አለት መሆኑንም በማከል።
ከ10 በላይ የአፍሪካ ሀገራት ከነጻነት በኋላ የሰንደቅ አላማቸውን ቀለም ከኢትዮጵያው አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ማዋደዳቸውም አድዋ የፈጠረው የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አካል ተደርጎ ይወሰዳል።
መላው ጥቁር ህዝብ እና ጭቁኖች የነጻነት ትግላቸው ፋና ወይም ብርሃን ያደረጉት አድዋ አህጉራዊ ብሎም አለም አቀፋዊ ድል ነው የሚባለውም ከዚህ መነሻ መሆኑን ነው ዶክተር ከተቦ የሚያነሱት።
አድዋ በኢትዮጵያ የሚገባውን ቦታ አግኝቷል ወይ?
በአድዋ ነጭ መሆን ሚዛን የሚደፋበት፤ ጥቁር ሆኖ መፈጠር አንገት የሚያስደፋበት አስከፊ ጊዜ ተሽሯል።
ድሉ በተለይ በአሜሪካ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ህዝቦች የዘመናት ጭቆናና የስነልቦና ቁስልን የሻረ ፤ የቆዳ ፍረጃንም ገደል የከተተ ነው።
በአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለማቀቁ አፍሪካውያን ያለው ስፍራም በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም የሚሉት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ፥ “አድዋ ከኢትዮጵያ ይልቅ በአፍሪካ የተሻለ ቦታ ሲሰጠው እናያለን” ይላሉ።
“አድዋ የመላው ኢትጵያውያን ድል እንዳልሆነ ሁሉ ባለፉት ሁለትና ሶስት አስርት አመታት አንዱ አሉላን ሌላኛው ባልቻን እየመረጠ ሲያከብር አይተናል፤ አሁንም አድዋን የማሳነስ ሙከራዎች ይታያሉ፤ በማይረባ ነገር እየተጨቃጨቅን ከታላቁ በዓል ልናገኝ የሚገባውን በረከት እያጣን” ነው ሲሉም ያብራራሉ።
አልጀሪያ በአሁኑ ወቅት ትልቅ የፓን አፍሪካኒዝም ሙዚየም እየገነባች መሆኑን የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር አየለ፥ “የድሉ ባለቤት ኢትዮጵያ ግን ከአድዋ በረከት ልትቋደስ ቀርቶ በአመት አንዴ የምታከብረውን በዓል ከንትርክ ነጻ አላደረገችውም” የሚል ቅሬታቸውን ያሰማሉ።
127ኛ አመቱን የያዘው የአድዋ ድል ጥልቅ ትርጉም ያለውና ከተጠቀምንበትም የአዲስ ከፍታ መነሻ ይሆናል ያሉት የታሪክ ምሁራን፥ በሚመጥነው አለማቀፋዊ ደረጃ ይከበር ዘንድም ይጠይቃሉ።