“አድዋን እንዘክር ከተባለ ያን ሁሉ ስንቅ፣ ሰራዊት ይዞ የሄደው የጋማ ከብት ሁሉ መታሰቢያ የሚያስፈልገው ነው”
“ዘረኛ ሳንሆን አድዋ ላይ የመታነው ዘረኝነት አሁን ተንሰራፍቷል” የሚሉት ተመራማሪው የበዓሉ የዘንድሮ አከባበር መንግስት ታሪክ ላይ ያለው አመለካከት መቀየሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል
“ፖለቲከኞቻችን ከታሪክ ይማሩ ታሪክን ግን የፖለቲካ ግብዓት አድርገው አጣመው አይጠቀሙ”
አል ዐይን አማርኛ ትናንት “አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸው ብቻ አይደለም የተዋጉት” በሚል ርዕስ ከታሪክ መምህር እና ተመራማሪው አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) ጋር ያደረገውን ቆይታ በዝርዝር ማስነበቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ተመራማሪው ኢትዮጵያውያን በአድዋ ለነጻነት ከመዋጋትም በላይ ቅኝ ገዢው አካል ይዞት የመጣውን የዘረኝነት አስተሳሰብ ድባቅ መምታታቸውን አስረድተዋል፡፡
ምንም እንኳ አድዋ እንዲህ ዓይነት መላው ጥቁርን ያኮራ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድ ያስቻለ ድል የተመዘገበበት ታላቅ የጦር አውድማ ቢሆንም ፖለቲከኞች በተለይም ከ1983 ዓ/ም ወዲህ የነበሩት ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ አዛብተው በማቅረባቸው ምክንያት ዘረኝነት በኢትዮጵያ ሊሰለጥን መቻሉንም ነው የገለጹት፡፡
ቀጥሎ በቀረበው የቆይታው ሁለተኛ ክፍልም እንዲህ ዓይነት የታሪክ መዛነፎች እንዴት ባለ መልኩ ሊታረቁ እንደሚችሉና ሌሎችንም ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን አንስተዋል፡፡
በሚከተለው መልኩ የተሰናዳውን ጥንቅር እንዲያነቡ ተጋብዘዋል፡፡
አል ዐይን ፡ ‘በዓሉ የካቲትን ሙሉ ይከበራል’ ተብሎ እየተከበረ ነው፡፡ ይህ መሆኑ የፖለቲከኛውን ልብ መግዛት ያሳይ ይሆን?
አበባው ፡ በእርግጥ አዎ፤ በመንግስት በኩል ትልቅ ለውጥ አለ፡፡ እንደ አድዋ ዓይነት በኢትዮጵያውያን ብቻም ሳይሆን በአፍሪካውያንም በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ዘንድ የጎላ ቦታ ያለው ታሪካዊ ሁነት ትልቅ ስፍራ ነው በሃገር ደረጃ የሚሰጠው፡፡ አንደኛ ብሄራዊ የታሪክ ትርክት (‘ናሽናል ሂስቶሪካል ናሬቲቭ’) ላይ ይገባል፡፡
ሁለተኛ ደግሞ የሚያስተምረው ነገር በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ሰፋ ባሉ ነገሮች ነው መከበር ያለበት፡፡
ለምሳሌ አንዳንድ ሃገራት ብሄራዊ ቀናቸውን በታሪክ ያለፉባቸውን አንዳንድ ቀናት ሰፋ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ አሜሪካውያኑ የካቲትን የጥቁሮች ታሪክ ወር ብለው ነው የሚያከብሩት፡፡ አድዋን እኛም ልንዘክረው ይገባ የነበረው በዕለቱ መድፍ ተኩሶ፤ አደባባይ ላይ ወጥቶ፤ ሸልሎ ፎክሮ ብቻ አልነበረም፡፡
አሁን ከተለመደው ወጣ ብሎ ረዘም ላለ ጊዜ በየክልሎቹ በሚካሄዱ ዝግጅቶች ተቋማት በተለይ ዩኒቨርስቲዎች በሚያደርጓቸው ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ የበዓሉን አከባበር የሚመራው በብሄራዊ ደረጃ ተቋቁሞ በፕሬዝዳንቷ በሚመራ ኮሚቴ ነው፡፡ ይሄ ቀላል አይደለም፡፡ ከታሪክ የምንማረው ነገር እንዳለ በማሰብ የተሰጠ ትኩረትም ነው፡፡ መንግስት ታሪክ ላይ ያለው አመለካከት መቀየሩንም ያሳያል፡፡
ወሩን ሙሉ የሚከበረው ያለንበት ወቅት ከሰላም ማስከበሩ፣ ከሱዳን፣ ከአባይ ውሃ እና ከግድቡ ጋር የተያያዙ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን የሚጠይቁ ችግሮች ያሉበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡
እያከበርን ያለነው ህልውናችንን ያስከበርንበትን፤ ዘረኝነትን የመታንበትን ድል ነው፡፡ አሁን ዘረኝነት ተንሰራፍቷል፡፡ አድዋ ላይ ዘረኝነትን የመታነው ዘረኛ ሳንሆን ነው፤ አንድ ላይ ተሰባስበን በአንድነት፡፡ ሃይማኖት አለየንም፤ ቀለም፣ ቋንቋ፣ ባህል አለየንም፡፡ የዛ ሁሉ አንድ ላይ መሆን ነው፡፡
ስለዚህ አድዋን በምናከብርበት ጊዜ ይሄን የተጠናወተንን ዘረኝነት በተለይ ፖለቲካው ያመጣብንን አሁንም በአንድነት ድል የምንመታበት መሆኑን መንግስት በራሱ አምኖበት ነው፡፡ ይሄ የተጠናወተንን ዘረኝነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፖለቲካ መድረካችንና አስተሳሰባችን በማውጣቱ ሂደትም ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
አል ዐይን ፡ አከባበሩ “አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ነው፤ ድሉን እንጂ ድሉን ያመጡትን አካላት ለማስታወስ አልተፈለገም፤ እነ ሚኒሊክ እና እነ ጣይቱን ረስቶ በዓሉን በተሟላ መልኩ ለማክበር አይቻልም” የሚሉ አካላት አሉ እርስዎ ምን ይላሉ?
አበባው ፡ ይሄ አድዋ በተከበረ ቁጥር ሁሌም ያለ ነው፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት ‘አድዋን ታከብራላቹ ግን ለአድዋ ምክንያት የሆኑትን ጀግኖች አትዘክሩም ይሄ ትክክል አይደለም’ በሚል ሲጠየቅ ነበረ፡፡
አድዋ ተከበረ ማለት ተወደደም ተጠላም ጣይቱ እና ሚኒሊክ መጠራታቸው አይቀርም፡፡ አድዋ ተዘከረ ማለት የእነሱ አስተዋጽኦ ተዘከረ ማለት ነው፡፡ ግን ደግሞ አንድ ነገር ልብ ማለት አለብን፡፡
አድዋ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ውጤት ነው ብለናል፡፡ ያ ሲሆን እነ ዳግማዊ ሚኒሊክ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኮንን፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ እነዚህና ሌሎችም ሁሌም ስማቸው በወጉ ተጽፎ ያሉ ናቸው፡፡
እንዲያውም አድዋን ስናከብር የእነዚህ የገዘፈና የተተረከ ምንም የማይሆን ስለሆነ መዘከር ያለባቸው መስዋዕት ሆነው የቀሩ ወታደሮች፣ ስንቅ ሲያደራጁ የነበሩ ሴቶች፣ ሃገር ጠባቂ ሆኖ ሃገር አማን አድርጎ ያቆየውን የጸለየውን ዱዓ ያደረገውን ሁሉ ነው፡፡ አድዋኮ ለሚያልፍ ወታደር አንድ ኩባንያ ውሃ የሰጠው ሁሉ የተሳተፈበት ነው፡፡
እና አንዳንድ ጊዜ አድዋን በጣይቱ እና በሚኒሊክ ብቻ ወስነን አንየው፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ትልቅ አስተዋጽኦ ነው፤ የታወቀ ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ግን ዝም ብሎ ሚኒሊክ አልተጠራም? ጣይቱ ለምን አልተጠራችም? እያሉ ብዙ መጨቃጨቅ አይገባም፤ አያስፈልግምም፡፡ ከተጠራ አልተጠራ አልፎ በአድዋ ውሎ ‘እከሌ ነው ያሸነፈው’ በሚል የሚጨቃጨቅ እኮ አለ፡፡ እዚህ ድረስ አንጨቃጨቅበት፡፡
ትልቁ ነገር እነዛን ጀግኖች የነበረውን ትውልድ እንዘክራቸው ነው፡፡ ከዚያም አልፎ አድዋን እንዘክር ከተባለ ያን ሁሉ ስንቅ፣ ሰራዊት ይዞ የሄደው የጋማ ከብት መታሰቢያ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በቅሎ፣ ፈረሱ፣ አጋስሱ ሁሉ መዘከር ያለበት ነው፡፡ እና በዚያ መንፈስ መመልከት እንጂ አንዳንድ ነገሮችን እየመዘዙ እያነወሩ አቃቂር እያወጡ ሌላ ነገር ማለቱ አይረባም፡፡
አል ዐይን ፡ በዓሉን ከማክበር ባለፈ አሉ የሚባሉ የታሪክ መዛነፎችን እንዴት እናስተካክል?
አበባው ፡ ታሪክን በሁለት መንገድ እንመልከተው ፤ ከመጀመሪያው ጀምሮ፡፡ ታሪክ የምንለው ነገር ያለፈ ድርጊት ነው፡፡ እና ያንን ያለፈ ድርጊት ከምንጮች፣ ከማስረጃዎች ተነስተን ነው ወደ ታሪክነት የምናመጣው፡፡ ያለፈ ነገር ሁሉ ደግሞ ምንጭ ወይም መረጃ ትቶ ላያልፍ ይችላል፡፡
ስለዚህ አሁን እኔ ታሪክን ዩኒቨርሲቲም ስማር በተለይ ማለት ነው ሙያዬ ሲሆን ትልቁ የተማርነው የታሪክ ፍልስፍና ምንድነው፤ ታሪክን ያለፈ ክስተትን መቶ በመቶ ቁልጭ አድርጎ ሊማወቅ አለመቻሉን ነው፡፡ መረጃዎች የሚነግሩን ምንጮች የሚነግሩንን ነው፡፡ ‘ሂስትሪ ኢዝ ሪኮንስትራክሽን’ ነው ምንለው እንጂ ያለፈ ክስተትን እንደገና የመመስረቱ የማወቁ ነገር፤ ከምንጭ እና ከመረጃ የሚነሳ ነው፡፡ መረጃ የሚሰጠንን ያህል ነው የምናውቀው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ከዛ ከተነሳን ታሪክ ሁልጊዜም አወዛጋቢ ነው፤ ከአወዛጋቢነት አይወጣም፡፡ ግን ሀቅ የሆነው ነገር ግን አያወዛግብም፡፡
ታሪክ ብዙ ጊዜ ምን?፣ መቼ?፣ ለምን?፣ እንዴት? እነዚህን ነው የሚመልሰው ፡፡ ምን ተደረገ? እና መቼ ተደረገ? አያጠራጥርም ብዙም፤ ሀቅ ስለሆነ፡፡ ለምን ተደረገ? እና እንዴት ተደረገ? ግን አወዛጋቢ ነው ሁል ጊዜ፡፡ ይህንን ውዝግብ ለሊቃውንቱ መተው ነው አንደኛው ነገር፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሁነኛ ከሆኑ የታሪክ መዛግብትና መጽሀፍት መነሳት ነው፡፡
አሁን እንግዲህ ታሪካችን አወዛጋቢ የሆነው በዚህ በታሪክ ጥናት ሁልጊዜ አወዛጋቢ ስለሚሆንና ሁሉን ማወቅ ስለማይቻል ሳይሆን ምንድነው ፖለቲከኛው ነው፡፡
አንዷን ታሪክ ነጥሎ እኮ ማንኳሰስ ይቻላል፡፡ የአንድን ሰው ለምሳሌ የህይወት ታሪክ በሁለት ነጥቦች ወይም በአንድ ነጥብ ብቻ ‘ዲማጎግ’ (ከእውነታው ይልቅ ለብዙሃኑ የልብ ትርታ ያደላ) ማድረግ ይቻላል፡፡ ወይም ደግሞ ነቅሰህ አውጥተህ ብቻ በሰውና በመላዕክት መካከል ያለ ልዩ ፍጥረት ልታደርገው ትችላለህ፡፡
ስለዚህ ፖለቲከኛው ከዚህ ነገር ይታቀብ፤ ታሪክን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ አይጠቀሙት ፡፡ ታሪክ ትልቅ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ታሪክ የሚተላለፍባቸው የተለያዩ መንገዶች እኛ ሀገር ስለሌሉ ነው እንጂ ሕዝቡም መስማት ያለበት የፖለቲከኛን ታሪክ አይደለም፡፡
አሁን ወደትልቁ ነገር እየተመጣ ነው፡፡ አንድ በርካታ ጊዜ ተሞክሮ ተከልክሎ የነበረው የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር በቅርብ ጊዜ መቋቋሙ ይፋ ይሆን ይመስለኛል ገና እየተቋቋመ ነው፡፡ ያ የሚፈጥራቸው መንገዶች አሉ፡፡ በተለይ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለሕዝቡ በቀላል ተደራሽ የሆኑ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ይሄ ነው፤ ይሄ ነው ይላል፡፡ ታሪክ ላይ ስህተትም በጎ ነገርም ሊኖር ይችላል፡፡ ያለፈው ትውልድ አይሳሳትም አይባልም፡፡
እምባቦ፣ ጨለንቆ፣ ሰገሌ ላይ እኮ እርስ በእርስ ተዋግተናል፡፡ አሁንም ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ነገር እኮ ሰሜን ዕዝ ላይ ተከስቷል፡፡ ይህ በሚቀጥሉት 20 ፣ 50 ምናምን ዓመታት እኮ ማነው ያጠፋው በሚል አወዛጋቢ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሰንዶ ማስቀመጥ ነው፤ ያኔ የሚኖረው ትውልድም ያነበዋል፤ ከውዝግብ ወጥቶ ይማርበታል ማለት ነው፡፡
እና ትልቁ ነገር ታሪክን በተለይ ለፖለቲካ ግብዓት ማድረግ፤ የመጀመሪያው እሱ ነው ስህተትን የሚያመጣው ማለት ነው፡፡ መማር ጥሩ ነው፤ ፖለቲከኛ ከታሪክ ቢማር ጥሩ ነው፡፡ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ የሚናገረው ነገር አለ “ታሪክን ማወቅ ጥሩ ነው፤ በተለይ ደግሞ ለቤተ መንግስት መኮንን” ይላል ካለፈው ይማራልና ብዙ ነገር፡፡ እና ፖለቲከኞቻችን ከታሪክ ይማሩ ታሪክን ግን የፖለቲካ ግብዓት አድርጎ፤ አጣሞ ወይንም ፈጠራ አድርጎ የሌለውን አለ ብሎ መናገሩ ግን ከፖለቲከኛ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፖለቲከኛ ትልቅ ኃላፊነት የሚሸከም ነው፡፡