ኢሰመኮ በአዲስ አበባ የአድዋ በዓል ላይ የህግ ጥሰት የፈጸሙ እንዲጠየቁ አሳሰበ
በአዲስ አበባ የጸጥታ ሀይሎች ሰዎችን ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ ምኒልክ አደባባይ እንዳይሄዱ ከልክለዋል ተብሏል
መንግሥት በበኩሉ ወደ በዓሉ ስፍራ እንዳይሄድ የተከለከለ ሰው የለም ማለቱ ይታወሳል
ኢሰመኮ በአዲስ አበባ የአድዋ በዓል ላይ የህግ ጥሰት የፈጸሙ እንዲጠየቁ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትናንት በአዲስ አበባ በተከበረው 127ኛው የአድዋ ድል በዓል ላይ የጸጥታ ሀይሎች ያልተመጣጠነ ሀይል ተጠቅመዋል ብሏል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዳሉት "የጸጥታ ሀይሎች በዓሉን ለማክበር የወጡ ግለሰቦችን መትተዋል፣ አስለቃሽ ጭስም ተኩሰዋል፣ እንዲሁም ፖሊስ ያልተመጣጠነ ሀይል ተጠቅመዋል" ብለዋል።
የአድዋ በዓል በሚከበርበት ምኒልክ ሀውልት አካባቢ የጸጥታ ሀይሎች ድርጊት አዛውንቶችን እና ህጻናትን ሳይቀር መጉዳታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ የተወሰደው የሀይል እርምጃ አላስፈላጊ እንደነበርም አክለዋል።
የጸጥታ ሀይሎች ዋነኛ ተግባር ዜጎችን ከማንኛውም ጥቃት መጠበቅ ቢሆንም ይህ እንዳልሆነ ጠቁመው በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ የጸጥታ ሀይሎች በህግ እንዲጠየቁም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ስምምነት መሰረት የጸጥታ ሀይሎች የሀይል አማራጮችን እንዳይጠቀሙ የተስማማችውን ህግ እንድታከብርም ዶ/ር ዳንኤል ጠይቀዋል።
በትናንትናው ዕለት የአድዋ በዓልን ለማክበር ወደ ሚኒልክ አደባባይ የተጓዙ የአይን እማኞች በጸጥታ ሀይሎች መደብደባቸውን እና በዓሉን እንዳያከብሩ መከልከላቸውን ለአል ዐይን መናገራቸው ይታወሳል።
የመንግሥት ኮሙንኬሽን ሚንስትር ዴዔታ አቶ ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው ወደ ሚኒልክ አደባባይ እንዳይጓዙ የተከለከለ አካል የለም በዓሉም በሰላም ተከብሯል ሲሉ አል ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል።
የመንግሥት ኮሙንኬሽን ትናት ምሽት ባወጣው መግለጫ “በምኒልክ አደባባይ የሚደረገውን በዓል ለመረበሽ የፈለጉ አካላት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረው ነበር” ብሏል።
እነዚህ አካላት የአደባባዩን በዓል መረበሽ ሲያቅታቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ሃይማኖታዊ በዓል ለመረበሽ ሞክረዋል ያለው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን፤ የጸጥታ አካላት ሑከት ፈጣሪዎችን ለማስታገሥ በሚያደርጉት ጥረት በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ በዓል ሊስተጓጎልና ለሃይማኖታዊ በዓል የመጡ ምእመናን መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል።
መንግሥት ይሄንን መሰል ተግባር መፈጸም እንደሌለበት ያምናል ያለው መግለጫው፤ ሁኔታውንም አጣርቶ በችግር ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ እንደሚወስድም ገልጿል።