አስተናጋጇ ኮትዲቯር እና ናይጄሪያ የፊታችን እሁድ ለዋንጫ ይፋለማሉ
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ተካሂደዋል።
በትናንት ምሽት ሁለት ሰዓት ናይጀሪያ ከደቡብ አፍሪካ፤ እንዲሁም ምሽት 5 ሰአት ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ኮቲዲቯር ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
ምሽት 2 ሰዓት ላይ በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ናይጄሪያ (ንስሮቹ) ደቡብ አፍሪካን (ባፋና ባፋናዎቹን) በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል።
በጨዋውም የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን፣ ዊሊያም ትሮስት ኢኮንግ በ67ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ መምራት ችለው የነበረ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካዎች በ90ኛው ደቂቃ ቲቦ ሞኮይና በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል።
በዚህም በመደበኛና በተጨማሪ የጨዋታ ሰዓት 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተዋል፡፡
በመለያ ምትም ናይጄሪያ ደቡብ አፍሪካን 4ለ2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ደርሳለች።
በመቀጠልም ምሽት 5 ሰዓት ላይ በኢቢምፒ ስታዲየም የአዘጋጇ ሀገር ኮትዲዮቫር እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መካል በተካሄደ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አስተናጋጇ ኮትዲቯር ዲሞክራቲክ ኮንጎን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜው ጨዋታ ደርሳለች።
ኮትዲቯር ሴባስቲያን ሄለር በ65ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ጨዋታውን በማሸነፍ የፍጻሜ ተፋላሚ ለመሆን በቅታለች።
ይህን ተከትሎም አስተናጋጇ ኮትዲቯር (ዝሆኖቹ) ከናይጄሪያ (ንስሮቹ) ጋ ለፍጻ የሚፋለሙ ይሆናል።
በዚህም የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ኮትዲዮቯር እና ሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ናይጄሪያ ቡድን የፊታችን እሁድ ከ በኢቢምፒ ስታዲየም ለዋንጫ ይፋለማሉ።
በትናንትናው ጨዋታ የተሸነፉት ደቡብ አፍሪካ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቅዳ እለት የሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ አቢጃን ላይ ይፋለማሉ።