የዝሆኖቹና ነብሮቹ፤ የንስሮቹና ባፋና ባፋናዎቹ ትንቅንቅ
በአፍሪካ ዋንጫ ለ16ኛ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው ናይጀሪያ ደጋግማ ያሸነፈቻትን ደቡብ አፍሪካ ትገጥማለች
አስተናጋጇ ኮቲዲቯር ደግሞ ከ1974 ወዲህ ለፍጻሜ ካልደረሰችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ትፋለማለች
የኮቲዲቯር እየተካሄደ የሚገኘው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ምሽት ሁለት ተጠባቂ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ምሽት ሁለት ሰአት ናይጀሪያ ከደቡብ አፍሪካ፤ ምሽት 5 ሰአት ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ኮቲዲቯር ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይፋለማሉ።
ንስሮቹ ከባፋና ባፋናዎች
ናይጀሪያ በአፍሪካ ዋንጫው 20 ጊዜ ተሳትፋለች፤ የዛሬ ምሽቱ ጨዋታም ለ16ኛ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችበት ነው። ይህም በ26 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ 16 ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችውን ግብጽ ክብረወሰን እንድትጋራ አድርጓታል።
ሰባት ጊዜ ለፍጻሜ የደረሱት ንስሮቹ በሶስቱ አሸንፈው ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወቃል።
ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫው አራተኛ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዋንን ነው ዛሬ ምሽት የምታደርገው።
ባፋና ባፋናዎቹ በ2000 ጋና እና ናይጀሪያ በጥምረት ባዘጋጁት 22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በናይጀሪያ ተሸንፈው ለፍጻሜ ሳይደርሱ መቅረታቸውን የካፍ መረጃ ያስታወሳል።
ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የምሽቱ ጨዋታ አራተኛው የሚሆን ሲሆን፥ ንስሮቹ በሶስቱ ማሸነፍ ችለዋል።
በቪክቶር ኦስሜን፣ ሉክማን እና ኢኮንግ የፊት መስመሯ የሚመራው የናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድን በኮቲዲቫሩ የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ የግብ ሙከራዎችን(19) በማድረግ ቀዳሚው ነው።
ባፋና ባፋናዎቹ ካስቆጠሯቸው ስድስት ጎሎች በግማሹ ተሳትፎ ያደረገው ቴምባ ዝዌንም በቡኬ ስታዲየሙ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ይጠበቃል።
ዝሆኖቹ ከነብሮቹ
የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታ ዋንጫ ወስዳ የማታውቀው ኮቲዲቯር ምሽት 5 ስአት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በማሸነፍ ለአቢጃኑ የፍጻሜ ጨዋታ ለማለፍ ትፋለማለች።
በ1992 እና 2015 የአፍሪካ ዋንጫን ያነሱት ዝሆኖቹ፥ የዛሬው ጨዋታ በአፍሪካ ዋንጫው ለ10ኛ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱበት ነው።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በበኩሏ ስድስተኛ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዋ ነው።
ንስሮቹ በስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇን ኢትዮጵያ በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሰው ጋናን 1 ለ 0 በመርታት ዋንጫውን ማንሳታቸው ይታወሳል።
ኮቲዲቯር እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአፍሪካ ዋንጫው ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተው ዝሆኖቹ በሁለቱ አሸንፈዋል፤ ንስሮቹ አንድ ጊዜ ረተዋል።
በ2015 ኢኳቶሪያል ጊኒ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫም ኮቲዲቯር በጥሎ ማለፉ ዲአር ኮንጎን 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።
ያለፉትን ሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ያዘጋጁና ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች ምንም ጎል ሳያስቆጥሩ ለፍጻሜው አልደረሱም፤ ጋና በ2008 (በካሜሮን 1 ለ 0) ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ በ2015 (በጋና 3 ለ 0) እንዲሁም ካሜሮን በ2021 (በግብጽ በመለያ ምት) ተሸንፈው ለፍጻሜ መድረስ አልቻሉም።
ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫውን አዘጋጅታ ለፍጻሜ የደረሰችው ግብጽ ናት(በ2006)።